ከ10 ሚሊየን ዶላር በላይ የተገነባው ሲካ አቢሲኒያ የግንባታ ኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 2፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ10 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የሲካ አቢሲኒያ የግንባታ ኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካ ዛሬ ተመርቋል።

ዓለም ገና ወለቴ አካባቢ የተገነባው ፋብሪካው በሶስት ዋና ምርቶች 16 የግንባታ ኬሚካሎችን እንደሚያመርት ተነግሯል።

ከሚያመርታቸው ኬሚካሎች ውስጥ የግንባታ ማጣበቂያዎች፣ የእድሳት እና ጥገና፣ ለወለልና ጣራ ስራ የሚያገለግል ኬሚካሎች ይገኙበታል ነው የተባለው።

በፋብሪካው የምርቃ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ፥ ፋብሪካው በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የግንባታ ኬሚካሎችን የሚያመርት ነው ብለዋል።

በዚህም ከዚህ ቀደም ከውጭ ይመጡ የነበሩ የግንባታ ኬሚካሎችን በቅርበት ለማግኘት እና የውጭ ምንዛሬን ለማዳን ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

zufan.jpg

ፋብሪካው የኬሚካል ማምረቻ ብቻ ሳይሆን የራሱ የስልጠና ማዕከል እና የኬሚካል መፈተሻ ቤተሙከራዎችን ያካተተ መሆኑ፥ ከፍተኛ የእውቀት ሽግግር ለመፍጠር እንደሚያግዝ ነው አቶ ፍፁም የገለፁት።

የኬሚካል ኢንዱስትሪውን በቀጣይ ለማስፋፋትም፥ እድል የሚፈጥርና ግንባታዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ለማድረግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ ፔትሪ ሶር ግሪንዳኑ በበኩላቸው፥ ፋብሪካው አሁን ከሚያመርታቸው በተጨማሪ ሌሎች የግንባታ ኬሚካሎችን እንደሚያመርት ጠቁመዋል።

የሚያመርታቸውን ኬሚካሎች ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ነው የተናገሩት።

ተቀማጭነቱን ስዊዘርላንድ ያደረገው ሲካ አቢሲኒያ የተባለው የግንባታ ኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታው ለመጠናቀቅ ከ1 ዓመት ከ6 ወር በላይ ጊዜ መውሰዱ ተመላክቷል።

 

 

በዙፋን ካሳሁን