አየር መንገዱ የአራት ኮከብ ደረጃ የምስክር ወረቀት አገኘ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 3 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስካይትራክስን የአራት ኮከብ ደረጃ የምስክር ወረቀት አገኘ፡፡

አየር መንገዱ ለንደን በተካሄደው ልዩ ስነስርዓት ከታዋቂው የአየር ትራንስፖርት ደረጃና ጥራት መዳቢ ድርጅት የምስክር ወረቀቱን አግኝቷል።

በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤድዋርድ ፕላይስትድ እንዳሉት፥ አየር መንገዱ የሀገሪቱን ባህልና እንግዳ ተቀባይነት የማስተዋወቅ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ነው፡፡

አየር መንገዱ ከአምስት ዓመታት በፊት የነበረውን አገልግሎቱን ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ መቀየሩንም ነው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በበኩላቸው፥ የአራት ኮከብ እውቅና የምስክር ወረቀቱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

ደንበኛ ተኮር አየር መንገድ እንደመሆኑም የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች እውቅና ማግኘታቸው አስደሳች መሆኑንም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የተናገሩት፡፡
ለአየር መንገዱ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ከ12 ሺህ በላይ ሰራተኞችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካሁን በፊትም የስካይ ትራክስን በአፍሪካ ምርጥ የአየር መንገድ ስታፍ ሽልማት ለሁለት ጊዜ ያሸነፈ ሲሆን፥ በቅርቡም በአፍሪካ ምርጥ ዓለም ዓቀፍ አየር መንገድ ሽልማት መውሰዱን ቮይስ ኦንላይንን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።