10 ዓመት ያስቆጠረው የሙሉ መሶብ ፉድስ አክሲዮን ማህበር ያለበትን ደረጃ ማወቅ አልቻልንም - ባለ ድርሻዎች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከ450 በላይ አባላትን ይዞ ከ10 ዓመት በፊት የተቋቋመው የሙሉ መሶብ ፉድስ አክሲዮን ማህበር ያለበትን ደረጃ ማወቅ አልቻልንም ይላሉ ባለአክሲዮኖች።

ቅሬታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያቀረቡት የአክሲዮን ማህበሩ አባላት፥ ቦርዱ የሙሉ መሶብ ፉድስ አክሲዮን ማህበር ያለበትን ደረጃ ሊያሳውቀን አልቻለም ይላሉ።

አክሲዮን ማህበሩ ተከራይቶ ይሰራበት ከነበረው ቤት በመልቀቁና ጽህፈት ቤቱም በመዘጋቱ አድራሻውን ማግኘት አልቻልንም ነው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢ አባላቱ።

አባላቱ እንደሚሉት ከአክሲዮን ማህበሩ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ከአራት አመት ወዲህ ተቋርጧል።

የሙሉ መሶብ ፉድስ አክሲዮን ማህበር ቦርድ በበኩሉ፥ አክሲዮኑ ከሁለት ዓመት በፊት በኪሳራ ምክንያት እንዲዘጋ የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ከአባላቱ ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋርጫለሁ ብሏል።

የአክሲዮን ማህበሩ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ኢንጅነር ሽመልስ አድማሱ፥ አክሲዮኑ በአባላቱ እንደቀረበው በድንገት የተሰወረ አይደለም ይላሉ።

ጠቅላላ ጉባኤ ተደርጎ ማህበሩ ኪሳራ ውስጥ መግባቱንም ለአባለቱ አሳውቀናል ነው የሚሉት።

አባላቱ ግን በተደረገ ጠቅላላ ጉባኤ ማህበሩ አደጋ ላይ መውደቁ በቦርዱ ከመጠቀሱና ድርጅቱን ለመታደግ 5 አባላት ያለው ኮሚቴ ተዋቅሮ ስራ ከመጀመሩ ውጭ ያሳወቀን ነገር የለም ይላሉ።

የንግድ ሚኒስቴርም ቦርዱ የማህበሩን ወጭ እና ቀሪ በወጭ ኦዲት አስመርምሮ ለአባላቱ እስካላሳወቀ ድረስ ከአባላቱ ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋርጫለሁ ማለት እንደማይችል ይገልጻል።

በንግድ ሚኒስቴር የአክሲዮን እና የንግዱ ዘርፍ ማህበራት ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ አለሙ፥ አክሲዮን ማህበሩ ሙሉ በሙሉ ፈረሰ የሚባለው በውጭ ኦዲት ያለውን ካፒታል አስመርመሮ ኪሳራውንም ትርፉንም ለአባላቱ ሲያሳውቅ መሆኑን ይገልጻሉ።

የንግድ ሚኒስቴር ቦርዱ በውጭ ኦዲት እንዲያስመረምር ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ቢያቀርብም እሰካሁን በቦርዱ በኩል ያለዉ ተነሳሽነት አነስተኛ ነው።

አሁን ላይም እንዲህ ያለውን ተግባር እንዲያከናውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለቦርዱ ጥሪ ማቅረቡን የተናገሩት አቶ ዮሴፍ፥ ይህ ካልሆነ ግን ለህግ ለማቅረብ እንደሚገደዱ አንስተዋል።

የሙሉ መሶብ አክሲዮን ማህበር ምክትል ሰብሳቢ ዶከተር ኢንጅነር ሺመልሰ አድማሱ፥ ቦርዱ በወቅቱ ኦዲት አለማስደረጉ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በቅርቡ የቦርድ አባላትን በመሰብሰብ አክሲዮን ማህበሩ በውጭ ኦዲት እንዲያስደርግ እናደርጋለን ብለዋል።

ይህን የኦዲት ሪፖርት ተከትሎም ለአክሲዮን ማህበሩ አባለት ትርፍ እና ኪሳራዉን እናሳውቃለን ሲሉም ተናግረዋል።

 

በተመስገን እንዳለ