የካናዳ ኩባንያ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመክፈት ጥናት እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 11፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢነርጂ ኮ-ኢንቨስት ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪና የሀይል መሙያ (ቻርጀር) መገጣጠሚያ ፋብሪካ ሊከፍት ነው።

ኩባንያው ፋብሪካውን ለማቋቋም የሚያስችል የኢንቨስትመንት አዋጭነት ጥናት በማካሄድ ላይ እንደሚገኝም ተነግሯል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል ኢነርጂ ኮ-ኢንቨስት ኮርፖሬሽን ባለቤት ጆርዳን ኦክስሌይን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

doc_1.jpg

ዶክተር አክሊሉ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ ታዳሽ ሃይል የሚጠቀሙና በዘርፉ የሚሰማሩ ኩባንያዎችን እንደምታበረታታ ገልጸዋል።

ይህም ሀገሪቱ ከያዘችው በአረንጓዴ ልማት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት ከያዘችው አገራዊ ፖሊሲ የሚመነጭ መሆኑን ተናግረዋል።

ኩባንያው የያዘው እቅድ ከአገሪቱ የልማት ፖሊሲ ጋር የሚጣጣም መሆኑንም አስረድተዋል።

ኩባንያው ወደ ስራ ቢገባ በስራ እድል ፈጠራና በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውና ለዚህም መንግስት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የኩባንያው ባለቤትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ጆርዳን ኦክስሌይ በበኩላቸው ኩባንያቸው ጥናቱን ሲያጠናቅቅ በኢትዮጵያ መዋለ ንዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያላት የአረንጋዴ ኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲና እያደገ ያለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ተመራጭ እንዳደረጋትም ተናግረዋል።

ኩባንያው ጥናቱን ጨርሶ ወደ ስራ ለመግባት ከወሰነ ከእነሙሉ የፋይናስ አቅሙ እንደሚመጣም ገልጸዋል።

የሚመረቱት ተሽከርካሪዎች ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለአገር ውጭ ገበያ እንደሚቀርቡም አስረድተዋል።

ኩባንያው በፖላንድ፣ ቱርክ፣ ካናዳ፣ ካሪቢያንና የተለያዩ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ፕሮጀክቶችን አከናውኗል።

በቀጣይ በአፍሪካ ለሚኖረው ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያን እንደማዕከል ለመጠቀም ማቀዱንም ዋና ስራ አስፈጻሚው መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።