በታህሳስ ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ባለበት ይቀጥላል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የንግድ ሚኒስቴር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ከአውሮፕላን ነዳጅ በስተቀር ባለበት እንዲቀጥል መወሰኑን አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋው ከነገ ህዳር 28 ቀን እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ባለበት እንዲቀጥል መወሰኑን አስታውቋል።

የዓለም ነዳጅ ዋጋ መዋዥቅ በሀገር ውስጥ ገበያ ላይ አለመረጋጋት እንዳይፈጥር፥ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋው ባለበት እንዲቀጥል ተወስኗል ነው ያለው።

ነገር ግን የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ በህዳር ወር ሲሸጥ ከነበረበት 19 ብር ከ61 ሳንቲም ከፍ ብሎ በታህሳስ ወር በ21 ብር ከ06 ሳንቲም እንዲሸጥ መወሰኑንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

በአለም ገበያ ላይ የሚኖረውን የነዳጅ ዋጋ መነሻ በማድረግም እንደአስፈላጊነቱ በነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ላይ ማስተካከያ ሊደረግ ይችላል ብሏል።