በኢትዮጵያ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ መኖሩን የሞሮኮ ኩባንያዎች ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ያለው የኢንቨስትመንት አማራጭ ሰፊና ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን የሞሮኮ ኩባንያዎች ገለፁ።

በአዲስ አበባ ከትናንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት እየተካሄደ በሚገኘው የአግሪ ቢዝነስ ፎረም ላይ ሞሮኮን በመወከል 13 ኩባንያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ልዑኩ የቢዝነስ አጋርነት ለመፍጠር እና በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት ሁኔታ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ተወያይቷል።

የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህብራት ምክር ቤት አማካሪ አቶ አዲሱ ተክሌ፥ የሁለቱ ሀገራት ኩባንያዎች የቢዝነስ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በፈረንጆቹ 2016 በኢትዮጵያ ያሉ የቢዝነስ አማራጮችን እና ምቹ ሁኔታዎችን ለማየት 72 የሞሮኮ ኩባንያዎች በሶስተኛው የኢትዮጰያና የሞሮኮ የቢዝነስ ፎረም ላይ መሳተፋቸውን አስታውሰዋል።

በዘንድሮው ፎረም እየተሳተፉ ከሚገኙ ክባንያዎች የአንዱ ተወካይ የሆኑት የኑስ ቾክረላህ፥ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ ምርቶችን ከሀገር ውስጥ የንግድ አጋሮች ጋር በመሆን አምርቶ ለገበያ የማቅረብ ፍላጎት እንዳለው ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ነዝሃ አሎዊ ምሃመዲ፥ በግሉ ዘርፍ ያለው ትስስር የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እየተጠናከረ የመምጣቱ መገለጫ ነው ብለዋል።
በፈረንጆቹ 2016 ህዳር ወር የሞሮኮው ንጉስ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት፥ ለሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱንም ነው የገለፁት።

መረጃውን ያገኘነው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።