የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላት የ1 ቢሊዮን 119 ሚሊየን ብር ቦንድ ገዝተዋል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአገር መከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የ1 ቢሊዮን 119 ሚሊየን ብር ቦንድ ገዝተዋል።

አባላቱ ቦንዱን የገዙት የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ድጋፍ በሰባት ዙር ከደመወዛቸው በመክፈል ነው።

የሠራዊቱ አባላት የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የህዳሴው ግድብ ግንባታ ያለበትን ደረጃና ሲጠናቀቅ የሚኖረውን ጠቀሜታ አስመልክቶ ለመከላከያና ፖሊስ ሠራዊት አባላት ጋር ተወያይቷል።

የስዕልና የፎቶ አውደ ርዕይም አካሂዷል።

በውይይቱ የተሳተፉት የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላት እንደገለጹት፥ የህዳሴው ግድብ ግንባታ የቦንድ ግዢ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ግዢ ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

የግድቡ ግንባታ በአገሪቱ የጋራ መግባባትን የሚፈጥርና ለህዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚኖረው ሚና የጎላ በመሆኑ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያረጋገጡት።

የፌዴራል ፖሊስ አባላቱ ሰባተኛ ዙር የቦንድ ግዢ እያከናወኑ ሲሆን የ220 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የ89 ሚሊየን፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ሲቪል ሰራተኞችን ጨምሮም ከ810 ሚሊየን ብር በላይ የቦንድ ግዢ ማከናወናቸው ነው የተገለጸው።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላቱ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የ24 ሠዓት ጥበቃ ከማድረግ ባሻገር ለ7ኛ ዙር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ በማድረግ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆናቸው የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የግድቡን ኃይል የማመንጨት አቅም ከ5 ሺህ 250 ወደ 6 ሺህ 450 ሜጋዋት ማሳደግ መቻሉንና የግንባታው 64 በመቶ መጠናቀቁንም አንስተዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ