በመዲናዋ ምክኒያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ከ4 ሺህ በላይ የንግድ ድርጅቶች ታሽገዋል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲሰ አበባ ከተማ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ሰበብ በማድረግ በሸቀጦች ላይ ምክኒያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 4 ሺህ 22 የንግድ ድርጅቶችን ማሸጉን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በመዲናዋ እየተከሰተ ያለውን የሸቀጦች እጥረትና የዋጋ ጭማሪ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ዳመጠው አበበ እንደገለፁት፥ ቢሮው ባደረገው ክትትል አብዛኛው ኅብረተሰብ በሚጠቀምባቸው ሸቀጦች በተለይም በግብርና ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ የዋጋ ጭማሪው ጎለቶ ታይታል።

በመሆኑም በእነዚህ ነጋዴዎች ላይ ከቃል እስከ ማሸግ የደረሰ እርምጃ መወሰዱን ሃላፊው ተናገረዋል።

በተጨማሪም ከ7 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነጋዴዎች የፅሁፍ፤ ከ8 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ደግሞ የቃል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

ነጋዴዎቹ ሸቀጦቹን ወደ መደበኛ ዋጋቸው እንዲመለሱ ክትትል እየተደረገ መሆኑን የገለፁት አቶ ዳመጠው፥ እርምጃውም የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል።

 

 

 በታሪክ አዱኛ