ኢትዮጵያና ማልታ ያለተጨማሪ ቀረጥ ምርቶችን ለማስገባት ተስማሙ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 8 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ማልታ ያለተጨማሪ ቀረጥ ምርቶችን ለማስገባት ተስማምተዋል።

ስምምነቱ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ያሳልጠዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ስምምነቱ በኢትዮጵያ ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማሳየት በማልታ በተካሄደ የቢዝነስ የምክክር መድረክ ላይ የተደረሰ ነው ተብሏል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል የተመራ የልዑካን ቡድን በምክክር መድረኩ ተሳትፏል።

ሚኒስትር ዲኤታው በሃገሪቱ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችና እድሎች ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሚኒስትር ዲኤታው የተመራ የልዑካን ቡድንም ከማልታ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካርሜሎ አቤላ ጋር የሃገራቱን የንግድና ኢኮኖሚ ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል።

ቡድኑ በማልታ የሚገኙ ታላላቅ የግብርና እና የምግብ ማቀነባበሪያ ኩባንያዎችን እንዲሁም ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ሆቴልና የቱሪዝም ዘርፎችን ጎብኝቷል።

የምክክር መድረኩ ሮም በሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ እንዲሁም በማልታ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የንግድ ሚኒስቴር በጋራ የተዘጋጀ እንደነበር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።