የመጀመሪያው ዙር የ40/60 የንግድ ቤቶች ጨረታ ውጤት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2010፣ (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ እንደገለጸው የመጀመሪያው ዙር የ40/60 የንግድ ቤቶች ጨረታ ውጤት ይፋ ሆኗል።

በመዲናዋን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም በመንግስት የተገነቡ ቤቶች እስከ 2ኛ ወለል ድርስ ለንግድ አገልግሎት የተገነቡ በመሆናቸው ኢንተርፕራይዙ ለተጠቃሚዎች በጨረታ እያስተላለፋቸው ነው ተብሏል።

 በዚሁ ፕሮግራም በሰንጋ ተራና ክራውን ሳይቶች በተገነቡ 305 የንግድ ቤቶች ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ.ም ግልጽ ጨረታ የወጣ መሆኑ ይታወሳል።

በዚህም በሰንጋ ተራ 88 እና በክራውን 36 የንግድ ቤቶች ጨረታ አሸናፊዎች የታወቁ ሲሆን፥ በቀሪዎቹ የንግድ ቤቶች ላይ ተጫራቾቹ መስፈርት ያላሟሉና ተወዳዳሪ ያልቀረበ እንደሆነም ታውቋል።

በጨረታው የቀረበው ከፍተኛ ዋጋ በካሬ ሜትር 171 ሺህ አንድ ብር ከ50 ሣንቲም ሲሆን ዝቅተኛው 19 ሺህ 501 ብር ከ01 ሣንቲም እንደሆነም ተገልጿል።

ለአገልግሎት ዝግጁ የሆኑት እነዚህ የንግድ ቤቶቹ ከ70 እስከ 390 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ሲሆኑ፥ የመጸዳጃና የመኪና ማቆሚያ ቦታም አላቸው ነው የተባለው።

 

 

 

በሶዶ ለማ