የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን የተዳከመው በ15 በመቶ ቢሆንም የግንባታ ግብዓቶች የዋጋ ጭማሪ ከ51 በመቶ በላይ ሆኗል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2010፣ (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጥቅምት ወር የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ ከተካሄደ በኋላ በግንባታ ግብዓቶች ላይ የተከሰተው የዋጋ ጭማሪ ከ51 በመቶው በላይ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና የደረጃ አንድ ተቋራጮች ማህበር ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ በቀረበ ጥናት ላይ ነው ይህ የተገለፀው።

በብረት ምርቶች ላይም የውጭ ምንዛሬ ከመወሰኑ በፊት ከነበረው የ76 በመቶ የዋጋ ጭማሪ እንደተከሰተ ጥናቱ አመልክቷል።

በዚህም በግንባታ ሂደት ላይ ከ30 በመቶው በላይ የዋጋ ንረት ሊከሰት እንደቻለ ጥናቱ አመልክቷል።

ይህን ተከትሎም የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያው ከመወሰኑ በፈት ውል በወሰዱ የግንባታ ተቋሯጮች ላይ የ31 ነጥብ 64 በመቶ የግንባታ ግብዓቶች ጭማሪ እንደተከሰተ ታውቋል።

በተመሳሳይ የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ ከመወሰኑ በፊት ውል በወሰዱ ውሃና ኤሌክትሪክ ስራዎች ደግሞ የ61 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ ታይቷል ተብሏል።

በዚህም ግንባታዎች እንዲቋረጡ እና የሀገር ውስጥ የግንባታ ተቋራጮች ከገበያው እንዲወጡ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያው ሲካሄድ ከግንባታ ጋር ተያይዞ የወጡ ህጎች ተፈፃሚ አለመሆናቸው ችግሩን እያባባሰው እንደሆነም ተነስቷል።

ባለፈው ጥቅምት ወር የወጪ ንግድን ለማበረታታት የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን በ15 በመቶ ተዳክሞ ተግባራዊ መደረግ እንደጀመረ ይታወሳል።

የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን መዳከም የዋጋ ንረትን እንዳያስከትል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ጥብቅ አድርጎ እንደሚተገበርም አስታውቆ ነበር።

በዙፋን ካሳሁን