81 ቢሊየን ብር ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ተሰብስቧል

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 16፣ 2007 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሰልጣን በ2007 በጀት አመት ከሰበሰብኩት አጠቃላይ ገቢ 81 ቢሊየን ብር ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ያገኘሁት ነው አለ።

ይህም ባለሰልጣኑ በበጀት አመቱ ከሰበሰበው ጠቅላላ ገቢ 65 በመቶውን ይሸፈናል።

ባለስልጣኑ ከከፍተኛ ግብር ከፋዮችና ባለደርሻ አካላት ጋር  በታክስ አስተዳደር አፈፃፀምና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ባለስልጣኑ በበጀት አመቱ ከሰበሰበው ገቢ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ነው የተነገረው።

ይሁን እንጂ ባለስልጣኑ ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች እየተሰበሰበ ያለው ገቢ የሚጠበቀውን ያህል  ስኬታማ ነው ማለት አይቻልም ተብሏል።

በሀገሪቱ 1003 ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ያሉ ሲሆን ከአጠቃላይ ግብር ከፋዮች 3 በመቶውን ይይዛሉ።

በ2007 በጀት አመት ከተሰበሰበው 128 ነጥብ 32 ቢሊየን ብር 81 ነጥብ 16 ብሩ ከከፍተኛ ግብር ከፋዩ የተሰበሰበ ነው።

ከዚህም ውስጥ 53 ቢሊየን ብሩ ከሀገር ውስጥ ግብር ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን፥ ቀሪው ገቢ ደግሞ ከቀረጥ ነው የተሰበሰበው።

በውይይት መድረኩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት አለመጠቀም፣ ኮንትሮባንድ፣ በዘርፉ የሚስተዋለው የሰው ሀይል እጥረት እና የግብር አሰባሰብ ስርአቱ ወጥነት የጎሰለው መሆኑ በክፍተት ተነስቷል።

ግብራቸውን በትክክልና በአግባቡ በመክፈል ለሌሎች አርአያ ናቸው የተባሉ 48 የግል ከፍተኛ ግብር ከፋዮችና 10 የመንግስት የልማት ድርጅቶችም ዛሬ ሽልማት ተበረክቶላቸዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም ስለ ግብር ግንዛቤ ፈጥሯል በሚል ሽልማት ተበርክቶለታል።

በታደሰ ብዙአለም

 


የተጫነው፡- በፋሲካው ታደሰ