በስሙ ምክንያት 40 የስራ ማመልከቻዎች ውድቅ የተደረጉበት ኢንጅነር ሳዳም ሁሴን

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ህንዳዊው ሳዳም ሁሴን በታሚል ናዱ ኖሩል ዩኒቨርሲቲ በባህር ሃይል ምህንድስና ትምህርት ዘርፍ በጥሩ ውጤት ተመርቆ ወጥቷል።

ከምረቃ በኋላ አብረውት የተማሩት የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ወደ ስራ አለም ሲሰማሩ እርሱ ግን በስራ ፍለጋ ብዙ ለፍቷል።

በዩኒቨርሲቲው በጥሩ ሁኔታ ስለመማሩ የትምህርት ማስረጃው ቢገልጽም፥ አያቱ ከ25 አመት በፊት ያወጡለት ስም ግን ለዚህ እንቅፋት ሆኖበታል።

ወጣቱ የትምህርት ማስረጃዎቹን በመያዝ ወደ 40 ለሚጠጉ ጊዜያት ቢያመለክትም “ሳዳም ሁሴን” የሚለው መጠሪያው ችግር ፈጥሮታል።

ሳዳም ሁሴን በሃገራቸው ህዝብ ላይ ጭቆናን ፈጽመዋል ተብለው የተወነጀሉና የቀድሞው የኢራቅ መሪ መጠሪያ ስም ነበርና።

እናም ይህን ስም ይዘህ በኩባንያችን ውስጥ እንዴት ትሰራለህ በሚል ሁኔታ ደጃቸውን የጠናቸው ተቋማት ምሩቁን ለመቅጠር አሻፈረኝ ብለዋል።

በዚህ ሳቢያ የበርካታ ድርጅቶችን ደጅ ቢጠናም መጠሪያ ስሙን ጥላቻ ብቻ ለመቅጠር ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውንም ባለ ጉዳዩ ወጣት ይናገራል።

ላለመቅጠራቸው የሚሰጡት ምክንያት ደግሞ ከስሙ ጋር ተያይዞ በስደተኞች እና ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የሚመጣን ጥያቄ ፍራቻ ነው ይላል ወጣቱ።

ሁኔታው ደግሞ ሲመረቅ ተስፋን ሰንቆ ለወጣው ወጣት አስቸጋሪ ነበርና የፍትህ ተቋማትን ደጅ እንዲጠና አስገድዶታል።

በዚህም ስሙን ሳዳም የሚለውን ወደ ሰጂድ ለመቀየር አመልክቶ ይሳከለታል።

ያቀረበው ማመልከቻ ግን አሁንም ሌላ ጣጣ አምጥቷል፤ አዲሱ መጠሪያው የቀደሙት የትምህርት ማስረጃዎቹ ላይ መስፈር ነበረበትና ያን ማስተካከል በማስፈለጉ አሁንም የጓጓለትን ስራ በቶሎ እንዳያገኝ አድርጎታል።

ስለዚህም ይህን ማስተካከልና መወዳደር ትችላለህ ቢባልም ጉዳዮ ተጓቶ አሁንም መፈትሄ አላገኘም።

ይህ ጉዳይ ደግሞ በመጭው ሚያዚያ ወር መጨረሻ እልባት ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ጉዳዩን የያዘው ፍርድ ቤት የስራ ፈላጊው የቀደሙ መረጃዎች ላይ የሚሰፍሩ መጠሪያ ስሞች በሙሉ ሳጂድ ሁሴን በሚል እንዲቀየሩ ውሳኔ ይሰጥበታልና።

ያን ጊዜ ምናልባት የጠመመው እድል ይቃና ይሆናል፤ እስከዚያው በትዕግሰት መጠበቅ ግን የውዴታ ግዴታው ነው።

ሳዳም የሚለው ስም በኢራቅ እጅጉን የተጠላ እና የሚወገዝ ሲሆን፥ ኢንጅነሩም በዚህ ሳቢያ ሌሎች ገፈት ገማሽ ስመ ሞክሸዎች አሉት።

በዚህ ስም ሳቢያ በኢራቅ የሚገኙ የሺዓ ታጣቂዎች አግተው በጥይት እሩምታ ሊገሉት የነበረው ግለሰብ የተደቀነበት መሳሪያ በመወሰዱ ተርፏል።

በባግዳድ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት የሚማር ህጻን ደግሞ በስሙ ሳቢያ ከፍተኛ ውግዘትን እያስተናገደ ይገኛል።

ህጻኑ ልጅ ዘወትር በጓደኞቹ እንደሚጠላ፥ መዝሙር በሚመስል የጅምላ ጩኸት የውግዘት ድምጽን ያስተናግዳል።

እኩዮቹ አልፈው ተርፈውም እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ መላው ኢራቃውያን እንደሚጠሉት በአንድነት ይነግሩታል።

ይህ እንግዲህ ከሌላው ይለይ ዘንድ በቤተሰቦቹ በተሰጠው መጠሪያ ስያሜ ምክንያት ብቻ ነው።

ብቻ በኢራቅ ሳዳምን መሆን መፈጠርንም ያስጠላል ይላል፥ ሂንዱስታን ታይምስን ጠቅሶ የዘገበው ቢቢሲ።

ሳዳም ሁሴን ከ10 አመታት በፊት ቢሞቱም፥ መጠሪያ ስማቸው ግን ዛሬም እርግማን ሆኗል።