14 ሺህ ዶላር ከመንገድ ዳር ያገኘው ግለሰብ ለባለቤቱ መልሷል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካዋ ኦሃዮ ነዋሪ ከመንገድ ዳር ወድቆ ያገኘውን 14 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ለባለቤቱ እንዲመለስ ማድረጉ ተነግሯል።

ግለሰቡ ይህንን ለምን እንዳደረገ ተጠይቆም፥ “ገንዘቡን ለባለቤቱ የመለስኩት መልካም የሆነ ነገር በመስራት ለልጆቼ ጥሩ ምሳሌ ለመሆን ነው” ብሏል።

ጃክ ቦወርስ የተባለው ይህ ግለሰብ ገንዘቡን ባሳለፍነው ሳምንት ከመንገድ ዳር ያገኘ ሲሆን፥ በወቅቱም ቤተሰቦቹን በተሽከርካሪ ይዞ ዋሽንግተን ወደ ሚገኝ የመዝናኛ ስፍራ በመሄድ ላይ ነበር።

ጃክ ቦወርስ እንደተናገረው፥ መጀመሪያ ከመንገድ ዳር የወደቀውን ቦርሳ ስመለከት በውስጡ ላፕቶብ ኮምፒውተር የያዘ ነበር የመሰለኝ።

በኋላ ላይ ግን ከተሽከርካሪው ላይ ወርዶ ሲመለከት እንደጠበቀው በቦርሳው ውስጥ ላፕቶፕ ኮምፒውተር ሳይሆን በርካታ ባለ መቶ የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ኖቶችን ማግኘቱን ይናገራል።

ጃክ ቦወርስ ያገኘውን ገንዘብም ለዋሽንግተን ፖሊስ ወስዶ ያስረከበ ሲሆን፥ ፖሊስም የቦርሳውን ባለቤት አፈላልጎ በማግኘት ገንዘቡን አስረክቦታል።

ፖሊስ ከገንዘቡ ባለቤት አገኘውት ባለው መረጃም፥ የገንዘቡ ባለቤት ይህንን ሁሉ ገንዘብ የያዘው መኪና ለመግዛት ነበር፤ ሆኖም ግን የፈለገውን መኪና ሳይገዛ ተመልሷል።

ግለሰቡ ለፖሊስ እንደተናገረውም፥ በወቅቱ የፈለገውን አይነት ተሽከርካሪ በማጣቱ ገንዘቡን ከሚነዳው ተሽከርካሪ አናት ላይ እንዳስቀመጠው ረስቶት በማሽከርከር ላይ እያለ ነው የወደቀው።

ሆኖም ግን ምስጋና ለልጆቹ መልካም ነገርን ላስተምር፤ ጥሩ ስራ የመስራት ምሳሌ ልሁንላቸው ላለ አባት ይሁንና 14 ሺህ የአሜሪካ ዶላይ የጠፋበት ግለሰብ ገንዘቡን መልሶ ማግኘት ችሏል።

ምንጭ፦ www.emirates247.com