የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪው ለመመሪቂያ ፅሑፉ የሙዚቃ አልበም ሰርቶ አቅርቧል

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል በማዕረግ ለመመረቅ ጥናታዊ ፅሑፍ ሰርተው እያስገቡ ከሚገኙት ተማሪዎች አንዱ ግን የራፕ ሙዚቃ ማስረከቡ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡

የ20 ዓመቱ ተማሪ ስሙ ኦባሲ ሻው የሚባል ሲሆን፥ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ለመመረቂያ ጥናት የራፕ ሙዚቃ አልበም በማቅረብ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡

"ሊሚናል ማይንድስ" የሚል መጠሪያ ያለው የሻው የሙዚቃ አልበም፥ ከሌሎች የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች ያላነሰ ውጤት አስገኝቶለታል፡፡

በዚህም ኤ ማይነስ(A-) ውጤት በማምጣት በሚቀጥለው ሳምንት የማዕረግ ተሸላሚና ተመራቂ ይሆናል ነው የተባለው፡፡

ሻው "የራፕ አልበም ሰርቼ በመመረቂያ ፅሁፍነት ሳስገባ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተቀባይነት ይኖረዋል ብየ አላሰብኩም ነበር፤ ከዚህ ይልቅ ራፕ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ቦታ እንደማይሰጠው እና እኔም እንዳልሰራ ያደርጉኛል የሚል ግምት ነበረኝ" ብሏል፡፡

አሁን ግን አስገራሚው አልበሙ በሃርቫርድ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን በውስጡ 10 ዘፈኖችን አካቶ፥ በአሜሪካ ስለሚገኙ እና እንግልት እየደረሰባቸው ስላሉ ጥቁሮች መዝፈኑን ተናግሯል፡፡

ለዘፈኖቹ የሀሳብ መነሻ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከፍተኛ ዝና ከነበራቻ የጂኦፌሪ ቻውሰር የስነ ፅሁፍ ስራዎች እንደተዋሰም ጠቁሟል፡፡

የተማሪው የመመረቂያ ጥናት አማካሪ እና የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህሩ ጆሽ ቤል፥ ስለሻው ሲናገሩ በጣም ቁም ነገረኛ እና አስገራሚ የጥበብ ሰው ነው በሚል ገልፀውታል፡፡

በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ሲመረቁ ጥናታቸውን እንዲያቀርቡ፥ ባይገደዱም አብዛኞቹ የትምህርት ክፍሎች ግን በማዕረግ ለማስመረቅ ተማሪዎቻቸውን የፈጠራ ስራ ያሰሯቸዋል፡፡

ሻው የራፕ የሙዚቃ ኢንዱስትሪን ለማሳደግ ሲል ሙዚቃዎችን በቀጥታ ኢንተርኔት በነጻ እንደሚለቃቸው ገልጿል፡፡

ምንጭ፡-ኒውዮርክ ታይምስ