የአሜሪካዋ ሆኑሉሉ ከተማ በእግረኛ ማቋረጫዎች ላይ ስልክ የሚጠቀሙትን ልትቀጣ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የሃዋይ ግዛት መዲና በሆነችው ሆኖሉሉ ከተማ በጎዳና ላይ አነስተኛ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች መገልገል ሊታገድ ነው።

ከተማዋ መንገደኞች የእግረኛ ማቋረጫ ዜብራዎችን ሲጠቀሙ፥ ሞባይል፣ ታብሌት፣ ቪዲዮ ማጫዋቻ፣ ዲጅታል ካሜራ እና ላፕቶፕን መጠቀም እንዳይችሉ መከልከል የሚያስችላትን ውሳኔ አሳልፋለች።

ለዚህ የሚረዳውን እገዳም የከተማዋ ምክር ቤት 7 ለ 2 በሆነ ድምጽ ውሳኔ ሰጥቶበታል።

የምክር ቤቱ ውሳኔ ታዲያ ይህን ሲያደርጉ የተገኙ እግረኞች ይቀጡ ዘንድም የሚያደርግ ነው ተብሏል።

በውሳኔው መሰረት ህጉን ተላልፈው የእግረኛ ማቋረጫዎች ላይ በሞባይል ስልካቸው የሚነጋገሩ አልያም የጽሁፍ መልዕክት የሚላላኩ እግረኞች ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

ለዚህም ከ15 እስከ 99 የአሜሪካ ዶላር የሚከፍሉ ሲሆን፥ ተደራራቢ ጥፋት የሚያጠፉት ደግሞ እስከ 500 የአሜሪካ ዶላር የሚቀጡበት ሁኔታም ይኖራል ነው የተባለው።

ይህ የምክር ቤቱ ውሳኔ ፀድቆ ተግባራዊ ይሆን ዘንድም ለከተማዋ ከንቲባ ኪርክ ካልድዌል ቀርቧል።

ምክር ቤቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በእግረኛ ማቋረጫ ዜብራዎች ላይ፥ በዚህ ሳቢያ እግረኞች ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ የተመለከቱ ጥቆማዎች ከተማሪዎች ከደረሰው በኋላ ነው።

ተማሪዎቹ አብዛኛዎቹ መንገደኞች እግረኛ ማቋረጫዎች ላይ ከስልካቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ሳቢያ መንገዳቸውን ረስተው ለአደጋ እየተጋለጡ በመሆኑ ትኩረት ይሰጠው በማለት ለምክር ቤቱ አቤት ብለዋል።

ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ ከተሰበሰበ በኋላ በአብላጫ ድምጽ በመወሰን ህግ ሆኖ እንዲጸድቅ ወደ ከንቲባው መርቶታል።

ውሳኔው በከንቲባው ህግ ሆኖ ከፀደቀ ሁሉም የከተማዋ መንገደኞች በህጉ መሰረት ይመራሉ።

አንዳንድ ህግ አውጭዎች ግን መሰል ውሳኔዎችን ከማሳለፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል በማለት ሃሳቡን ኮንነውታል።

 

 

 

 

 

 

 


ምንጭ፦ ዩናይትድ ፕረስ ኢንተርናሽናል