በሜክሲኮ የተዘጋጀው የወንዶች የቁንጅና ውድድር ቆንጆ ወንድ ባለመገኘቱ ተሰረዘ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 12 ፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሜክሲኮ “የሚስተር ሞዴል ታባስኮ 2017” የወንዶች የቁንጅና ውድድር መስፈርቱን የሚያሟላ ቆንጆ ወንድ ባለመገኘቱ ተሰረዘ።

የውድድሩ አዘጋጅ ድርጅት ባወጣው መስፈርት ወንዶች በቁንጅና ውድድሩ ለመሳተፍ እድሜያቸው ከ17 እስከ 27 ዓመት መሆን ይኖርባቸዋል።

ቁመታቸው ቢያንስ 1 ሜትር ከ78 ሴንቲ ሜትር መስፈርት የተቀመጠለት ሲሆን፣ የፊት ገፅታቸው እና ተክለ ሰውነታቸው እጅግ የሚማርክ መሆን አለበት ይላል።

ከዚህም ባሻገር በእድሜያቸው ልክ የኮሌጅ ዲግሪ ወይም ሌላ የትምህርት ደረጃ ሊኖራቸው እንደሚገባ መረጃው ያሳያል።

Mr-Model-Tabasco2.jpg

እንግሊዝኛ ቋንቋን አቀላጥፎ መናገር እና ህጋዊ የጉዞ ሰነድ ሊኖራቸው እንደሚገባ እንዲሁም የተረጋጉ መሆን እንደሚጠበቅባቸው በመስፈርቶቹ ውስጥ ተዘርዝረዋል።

በዚህም መሰረት አወዳዳሪው ድርጅት ውድድሩ ከመድረሱ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ ከተመዘገቡ ወንዶች መካከል የተወሰነ የተሻሉ ያላቸውን ስድስት ብቻ መረጠ።

ሆኖም ድርጅቱ ከስድስቱ መካከል ለውድድሩ የሚመጥን ቆንጆ ወንድ አጥቻለሁ በሚል የቁንጅና ውድድሩን መሰረዙን አስታውቋል።

ወንዶቹ የቀረቡትን አካላዊ የቁንጅና መስፈርቶች ባለማሟላታቸው ነው ፕሮግራሙ የተሰረዘው።

በሜክሲኮ የታባስኮ ግዛት ሊካሄድ የነበረው ውድድር ውድቅ ቢሆንም፥ በቀጣይ ቆንጅ እና ተክለሰውነታቸው የሚያምሩ ወንዶችን በማሰስ ሌላ ውድድር እንደሚያዘጋጅ ድርጅቱ ገልጿል።

የሚስተር ሞዴል ታባስኮ 2017 ውድድር አዘጋጅ ድርጅት ለመወዳደር ያመለከቱ ወንዶችን ፎቶ ግራፍ በማንሳት በቴሌቪዥን ቢያስተዋውቅም ያወጣውን መስፈርት የሚያሟላ ወንድ አላገኘም።

በተለይም ለቁመት የተቀመጠው መስፈርት በጣም ለውስን ሰዎች ብቻ የሚያገለግል በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ያሉ ተወዳዳሪዎችም አሉ።

 

 

 

 

 

 

 

ምንጭ፦ ኦዲቲ ሴንትራል