በደቡብ ወሎ ዞን አንዲት ፍየል ሁለት ጭንቅላት ያላት ግልገል ወለደች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ወሎ ዞን ቦረና ወረዳ አንዲት ፍየል ሁለት ጭንቅላት ያላት ግልገል መወለዷ ተነግሯል።

በቦረና ወረዳ 019 መንደዩ ቀበሌ ልዩ ቦታው ታች ቦረቦር በሚባለው አካባቢ ባለቤትነቷ የአቶ ምረቱ ታረቀ የሆነች ፍየል መስከረም 27 2010 ዓ.ም ባልተለመደ መንገድ ከአንገቷ በላይ ሁለት አፍና አራት አይን ያላት ግልገል ወልዳለች።

የፍየሏ ባለቤት እንደገለጹት ፍየሏን ከገዛት ከ3 ወር በኋላ የወለደች ሲሆን፥ ግልገሏ ከተወለደች ጀምሮ መቆም አትችልም።

እንዲሁም በራሷ መጥባት ስላልቻለች ፍየሏን በማለብ በመጋት እስካሁን እየተንከባከቧት እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የቦረና ወረዳ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ባለሙያ ዶክተር ንጉሱ ብርሃኑ፥ ህብረተሰቡ በእንዲህ አይነት መንገድ ሲፈጠር ከፈጣሪ ቁጣ ጋር የማያያዝ ሁኔታ ይታያል ይላሉ።

ነገር ግን የፈጣሪ ቁጣ ሳይሆን ባልተለመደ መንገድ አልፎ አልፎ ሊከሰት እንደሚችል ጠቅሰዋል።

ከአንገት በላይ ሁለት አፍ እና አራት አይን ኖሯቸው የሚፈጠሩት ፈርትላይዝ መሆን ያለበት እንቁላል ሳይሰበር ሲቀር እና ሁለት የተለያዩ እንቁላሎች ለመንታ ታስበው ሳይሰበሩ ዘግይተው ማህጸን ላይ ሲጣበቁ የሚከሰትበት እድል እንደሚኖር ገልጸዋል።

በሰለሞን አበጋዝ