የዱባይ ፖሊሶች 300 ቶን የሚመዝን አውሮፕላን በገመድ 100 ሜትር በመጎተት አዲስ ክብረ ወሰን አስመዘገቡ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 56 የዱባይ ፖሊሶች ከ300 ቶን በላይ የሚመዝነውን ኤርባስ አውሮፕላን በገመድ ለ100 ሜትር ርቀት በመጎተት አዲስ ክብረ ወሰን አስመዘገቡ።

የዱባይ ፖሊስ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል አብዱላህ ከሊፋ አል ማሪ የፖሊስ አባሎቻቸው በውድድሩ አሸንፈው በድንቃድንቅ መዝገብ የሰፈሩበትን የምስክር ወረቀት ከዓለም የክብረ ወሰን ዳይሬክተር ሁዳ አል ከሰብ ተቀብለዋል።

ፖሊሶቹ በዱባይ አቅም በሚጠይቀው የሰውነት ማጎልመሻ ውድድር በገመድ የጎተቱት ግዙፍ አውሮፕላን ኤርባስ ኤ 380 የሚባለው ነው።

አውሮፕላኑ 302 ነጥብ 68 ቶን የሚመዝን ሲሆን፥ 56 ፖሊሶች 100 ሜትር ያህል ርቀት ጎትተውታል።

በዚህም ከዚህ ቀደም 100 ሰዎች 218 ነጥብ 56 ቶን የሚመዝን አውሮፕላን በመጎተት የያዙትን ክብረ ወሰን በማሻሻል የዱባይ ፖሊሶች በድንቃ ድንቅ መዝገብ ስማቸውን አስፍረዋል።

የዱባይ ጥንካሬን የሚጠይቀው የሰውነት ማጎልመሻ ውድድር ስፖርትን ባህል ለማድረግ እና ሰዎች የአካል ብቃት እንቅስቀሴ እንዲያደርጉ ለማነሳሳት ያለመ ነው።

የዱባይ ፖሊስ በዚህ ውድድር በድንቃድንቅ መዝገብ ላይ መስፈሩን ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነቱን ለመጨመር እንደሚያግዘው ዋና አዛዡ ተናግረዋል።

 

ምንጭ፦ www.emirates247.com