ቢሊየነሩ ቢል ጌትስ በአጋጣሚ ድሃ ቢሆኑ የሚሰማሩበትን የስራ መስክ ይፋ አድርገዋል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ በአጋጣሚ ያላቸውን ሃብት አጥተው ድሃ ቢሆኑ የሚሰማሩበትን የስራ መስክ ይፋ አድርገዋል።

ቢል ጌትስ በፎርብስ መፅሄት መረጃ መሰረት 89 ነጥብ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ሃብት በመያዝ ከዓለማችን ባለፀጎች መካከል አንዱ ናቸው።

የ62 ዓመቱ ቢሊየነር የማይክሮሶፍት ኩባንያ ተባባሪ መስራች መሆናቸውም ይታወቃል።

ከሰሞኑ አሁን ካሉበት የኑሮ እና የሃብት ደረጃ በተቃራኒው በድህነት ላይ ለመኖር አስገዳጅ ሁኔታ ቢኖር ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተጠይቀው ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

በዚህም ዊሊያም ቢል ጌትስ አሁን ያላቸው ግዙፍ ፀጋ ጠፍቶ በቀን ከ2 ዶላር ባነሰ ገቢ ለመኖር ቢገደዱ ሊሰሩ የሚችሉትን እቅድ ነው የተናገሩት።

ቢሊየነሩ በእቅድቸው መሰረት ድሃ ቢሆኑ በዶሮ እርባታ እንደሚሰማሩ ጠቁመዋል።

ለዚህም በጌትስ የበጎ አድራጎት ድርጅታቸው በዓለም ላይ በሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ድጋፍ ለማድረግ ሲሄዱ የተመለከቱት ሁኔታ እንዳነሳሳቸው ገልፀዋል።

ይኸውም በየሀገራቱ በድህነት የሚኖሩ ሰዎች የተለያየ አኗኗር እና የየዕለት ተግባር እንዳላቸው መገንዘባቸውን የጠቀሱት ቢል ጌተስ፥ በዶሮ እርባታ መሰማራት አነስተኛ ገንዘብ እና ቀላል ስራ የሚጠይቅ መሆኑን ነው ያነሱት።

“የተጠየቅኩት ጥያቄ ዛሬ በዓለማችን ከ1 ቢሊየን ያላነሱ ሰዎች በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚገኙበት ህይወት ነው፤ ይህን ጥያቄ ለመመለስ አንድ መልስ ብቻ ላይኖር ይችላል፤ በእርግጥ ድህነት ከቦታ ቦታ የተለያየ ነው።” ብለዋል።

ሆኖም የቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የቦጎ አድራጎት ስራ በድህነት ላይ ባሉ ሀገራት ከበርካታ ሰዎች ጋር ተገናኝቻለሁ፤ በዚህም አብዛኛዎቹ ሰዎች ዶሮ እያረቡ መለወጣቸውን ተመልክቻለሁ፤ ይህም በዶሮ እርባታ መሰማራት ቀላል እና ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተረድቻለሁ ነው ያሉት።

ዶሮዎች በድህነት ላይ ለሚኖሩ ዜጎች ለየዕለት ኑሮ የሚያስፈልግ ጥሩ ገቢን ያስገኛሉ፤ በፍጥነት ይራባሉ፤ በተለይ በምዕራብ አፍሪካ ደግሞ እስከ 5 የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያወጣሉ፤ ስለሆነም ድህነት ላይ ብኖር የማደርገው ዶሮ ማርባትን ነው ብለዋል።

ከዚህም ውጭ ዶሮዎች የሚያመርቱት እንቁላል በድህነት ላይ ለሚገኝ ቤተሰብ ጥሩ የተመጣጠነ እና ገንቢ ምግብ መሆኑም ስራውን እንድመርጠው ያስገድደኛል ሲሉ አብራርተዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ዶሮ ማርባት ሴቶች በየዕለቱ ለቤተሰባቸው የሚያስፈልጋቸውን ወጪ እንዲሸፍኑ እና በቂ ገቢ እንዲሰበስቡ አመቺ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

የቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ስራ ለበርካታ ድሃ ዜጎች ዶሮ እና ሌሎች እንስሳስትን አርብተው እንዲጠቀሙ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

በተለይም በአፍሪካ በድህነት የሚኖሩ ዜጎች ላይ የሚሰሩት በጎ ስራ ውጤታማ እንዲሆን ዶሮ ማርባት ላይ ማተኮራችውን ጠቁመዋል።

ፋውንዴሽኑ ከሰሃራ ቤታች የአፍሪካ ሀገራት በዶሮ ማርባት የተሰማሩ በድህነት ላይ የሚገኙ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ፥ ቋሚ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም በገጠሩ ክፍል የሚገኙ አርሶ አደሮች ጤናቸው የተጠበቁና ከአካባቢው የአየር ሁኔታ ጋር የተስማምተው የሚያድጉ የዶሮ ጫጩቶችን እንዲያረቡ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ቢል ጌትስ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ ሀገራት በምናደርገው ድጋፍ አሁን ጤናማ የዶሮ እርባታ ከጀመሩት 5 በመቶ ወደ 30 በመቶ ከፍ ለማድረግ ግብ ይዘናል ነው ያሉት።

 

 

 

 

ምንጭ፦ኢንዲፔንደንት