ህንዳዊው ግለሰብ በሱዳንና በግብፅ መካከል የሚገኝ መንግስት አልባ ስፍራ ላይ ራሱን ንጉስ አድርጎ ሰይሟል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 12፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ንጉስ የመሆን ፍላጎት ያለው ህንዳዊ ጉዞውን ወደ አፍሪካ በማድረግ በሱዳን እና ግብፅ መካከል የሚገኝ መንግስት አልባ ስፍራ ላይ ራሱን ንጉስ አድርጎ ሰይሟል።

በዚህ ብቻ ያላበቃው ግለሰቡ አባቱን ደግሞ የስፍራው ፕሬዚዳንት አድርጎ የሾመ ሲሆን፥ ይህንን ሹመትም የልደት ስጦታ አድርጎ ለአባቱ እንዳበረከተም አስታውቋል።

ሱያሽ ዲክሲት የተባለው ይህ ግለሰብ ንጉስ የመሆን ፍላጎቱን ለመወጣት ነው ከህንድ በመነሳት ባለቤት ወደሌለው በሱዳን እና በግብፅ መካከል ወደሚገኘው “ቢር ታዊል” ስፍራ የተጓዘው።

king_suyash_2.jpg

ሱያሽ ስፍራው የራሱ ግዛት መሆኑን ያወጀ ሲሁን፥ ራሱንም አዲስ የተመሰረተው የዲክሲት ስረወ መንግስት ንጉስ አድርጎ ሰይሟል።

“ከዛሬ ጀምሮም ራሴን ንጉስ ሱያሽ ቀዳማዊ በማለት እጠራለሁ” ሲል የተናገረው ሱያሽ፥ “ባለቤት አልባዋ ቢል አልታዊልም ስፍራም ከዚህ በኋላ ሀገሬ ነች” ብሏል።

“ቢል አልታዊልን ለማግኘትና ስፍራውን የኔ ለማድረግ አመቺ መንገድ ሳይኖር በበረሃ ውስጥ 319 ኪሎ ሜትሮችን ተጉዣለሁ” ሲልም ሱያሽ ተናግሯል።

“ሰፊ ቦታን የሚሸንፈው ይህ ስፍራ የየትኛውም ሀገር ክልል አይደለም፤ በዓለማችን ላይ ካሉ መሬቶች ውስጥ የሰው ልጅ መኖር የሚችልበት ነግር ግን የማንኛውም ሀገር አካል መሆን ያልቻለ ብቸኛው ስፍራ ይሄ ነው” ብሏል።

“በጥንት ስልጣኔ ህግ መሰረት እንድን ቦታ የኔ ነው ለማለት በላዩ ላይ ዛፎችን መትከል እና ማሳደግ ያስፈልጋል” ያለው ሱያሽ፥ ለዚህም ይረዳው ዘንድ የዛፍ ዝርያዎችን መትከሉን እና ውሃ ማጠጣቱን በመናገር “ስፍራው የኔ ነው” ብሏል።

king_suyash_3.jpg

ሱያሽ በቀጣይም አዲስ ያቋቋመው መንግስት በተባበሩት መንግስታት ድርጀት እውቅና እንዲያገኝ እንደሚሰራም አስታውቋል።

የዚህች ሀገር ዜጋ መሆን እና ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም ሰውም ወደ ስፍራው መጓዝ እንደሚችልም ገልጿል።

ምንጭ፦ www.alaraby.co.uk