ፍቅረኛዋን ለማስደሰት 30 ቀዶ ጥገናዎችን ያደረገችው ወጣት

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 28 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ቤሪ ኤን ጂ የ22 አመት የሆንግ ኮንግ ነዋሪ ስትሆን ለእይታ ማራኪና አማላይ ሆና ለመታየት በርካታ ቀዶ ጥገናዎችን ማድረጓን ትናገራለች።

ወጣቷ በ17 አመቷ የጀመረችው ቀዶ ጥገና የተሻለ ሆኖ ለመታየት ቢሆንም ከዚያ በኋላ ሱስ ሆኖባት ለበርካታ ጊዜያት ይህን ድርጊት መፈጸሟን ትናገራለች።

በተለያዩ አጋጣሚዎች የምትመለከታቸውን ምዕራባውያን ሞዴሊስቶችን ለመምሰል በሚል ቀዶ ጥገናውን ጀምራ እስከዛሬ 30 ጊዜ መሰራቷንም ነው የምትናገረው።

በወቅቱ በጀመረችው ቀዶ ጥገና መደሰት የጀመረችው ወጣት፥ በእድሜ ከእርሷ ከፍ ካለ ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት ከጀመረች በኋላ ደግሞ ድርጊቷን ይበልጥ ገፍታበታለች።

የፍቅር አጋሯ መልኳ እንደማያምርና እንደሚመለከታቸው ሴቶች ማራኪና አማላይ እንዳልሆነች በመንገር ያሳቅቃት እንደነበርም ገልጻለች።

እርሱን ለማስደሰትና የተሻለ ሆኖ ለመታየት በሚልም በሀያዎቹ እድሜዋ መጀመሪያ ላይ ከ20 የበለጡ ቀዶ ጥገናዎችን አድርጋለች።

የአይን ቅንድብና የአፍንጫ ቀዶ ጥገና እንዲሁም የምትመኘውን ክብ ፊት ለመያዝ ግንባሯ ላይ ህመም የሚፈጥሩ መርፌዎችን ተወግታለች።

የከንፈር፣ የጉንጭ፣ የአገጭ እንዲሁም የጡት ቀዶ ጥገናም አድርጋለች፤ ይህን ሁሉ ያደረኩት ግን እርሱን ለማስደሰትና ፍላጎቱን ለማሟላት ነበርም ትላለች።

ያን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍየ መጨረሻየ አላማረምና ግንኙነቴን አቋረጥኩም ትላለች ቤሪ።

ቀዶ ጥገናውን ከከወነች በኋላ እናቷን ጥየቃ ስታመራ፥ ከእናቷ ቁጣ እንደጠበቃት ገልጻለች።

ወላጅ እናቷ በወቅቱ አጉል አምራለሁ በሚል ሰበብ በተሰራችው ቀዶ ጥገና ሳቢያ ውበቷን እንዳበላሸችው ነግረውም ከሃሳቧ መለስ እንድትል ረድተዋታል።

እርሷም ባደረገቸው ነገር በመፀፀት አሁን ቀዶ ጥገናን በመቃወም መልዕክት ማስተላለፍ ጀምራለች።

በትንሽ እድሜዋ 30 ቀደ ጥገናዎችን ያደረገችው ቤሪ አሁን ላይ ወጣቶችን ከእኔ ተማሩ በሚል በዩ ቲዩብ መልዕክት አዘል ንግግሮችን ታስተላልፋለች።

የእድሜ እኩዮቿም ከዚህ ተግባር ታቅበው ራሳቸውን ከአላስፈላጊ አጋጣሚዎች ይጠብቁ ዘንድም ትመክራለች።

 

 


ምንጭ፦ ኦዲቲ ሴንትራል