ጃፓን ከእንጨት የሚሰራ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ልትገነባ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 13 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) አንድ የጃፓን ኩባንያ በአለም ረጅሙን ከእንጨት የሚሰራ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ለመገንባት ማሰቡን ገልጿል።

ኩባንያው በፈረንጆቹ 2041 ገንብቼ አጠናቅቀዋለሁ ያለው ከእንጨት የሚገነባው ሰማይ ጠቀስ ህንጻ፥ ባለ 70 ወለል ነው።

ህንጻውን ለመገንባትም 10 በመቶ ብቻ ብረት እጠቀማለሁ ብሏል የጃፓኑ ሱሚቶሞ ኩባንያ፤ 180 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር እንጨት ደግሞ ቀሪው የህንጻው አካል ይሆናል ነው የተባለው።

ህንጻው ተገንብቶ ሲጠናቀቅም ወደ 8 ሺህ መኖሪያ ቤቶች የሚኖሩት ሲሆን፥ ኩባንያው ምስረታውን በሚያከብርበት አመት የሚገነባው ህንጻ አጠቃላይ ወጭ ግን እጅግ በጣም ውድ ነው ተብሏል።

600 ቢሊየን የጃፓን የን ወይም 5 ነጥብ 6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ይጠይቃል።

350 ሜትር የሚረዝመው ህንጻ ታዲያ የተፈጥሮ አደጋዎችን እንዲቋቋም ተደርጎ እንደሚገነባም ኩባንያው ገልጿል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ጠንካራ የእንጨትና የብረት ኮለኖች የሚኖሩት ሲሆን፥ ይህ መሆኑ ደግሞ በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ ይረዳል ተብሏል።

የጃፓኖች እቅድ ታዲያ ከተፈጥሮ አደጋ በተጨማሪ የከባቢ አየር ብክለትን በመቀነስ ረገድ ከፍ ያለ ሚና እንዳለው ተጠቅሷል።

በኮንክሪትና በብረት የሚገነቡ ህንጻዎች ለከባቢ አየር መበከል 8 እና 5 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።

እንጨት በአንጻሩ ካርበንን አምቆ ስለሚይዝ በዚህ ረገድ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንዳለው ይነገራል።

ጃፓን በፈረንጆቹ 2010 ለህዝብ አገልግሎት በሚሰጡና ከሶስት ወለል በታች የሆኑ ህንጻዎችን እንጨት በመጠቀም መገንባት እንደሚገባ የሚደነግግ ህግ ማውጣቷ ይታወሳል።

አንዳንድ ሃገራትም ከተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ተያይዞ የእንጨት ህንጻዎችን ይገነባሉ።

በአሜሪካ ሚኒያፖሊስ ባለ 18 ወለል ከእንጨት የተሰራ ህንጻ ለቢሮ አገልግሎት እየዋለ ሲሆን፥ በካናዳ ቫንኮቨር ደግሞ ለተማሪዎች ማደሪያ የሚሆን ከእንጨት የተሰራ ህንጻ ይገኛል።

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ