መንትያውን በመተካት ከእስር ቤት ያመለጠው ፍርደኛ በቁጥጥር ስር ውሏል

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 13 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) አሌክሳንደር ጀፈርሰን ዴልጋዶ በፔሩ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት ማረሚያ ቤት 16 አመታትን በታራሚነት እንዲያሳልፍ የተወሰነበት ፍርደኛ ነው።

አሌክሳንደር ከወሲባዊ ጥቃትና ዝርፊያ ጋር በተያያዘ ነበር ለእስራት የተዳረገው።

የ28 አመቱ ወጣት ይህን የእስር ጊዜውን ሳይጨርስ ከአንድ አመት በፊት ከተራራማው እስር ቤት በማምለጥ ተሰውሮ የቆየበት መንገድ አነጋጋሪ ሆኗል።

ከአመት በፊት እርሱ ባለበት ማረሚያ ቤት መንትያ ወንድሙ ሊጠይቀው ይመጣል፤ በዚህ ወቅት ታዲያ አሌክሳንደር የወንድሙን ልብስ በመቀየር ነበር ከእስር ቤቱ ያመለጠው።

ለዚህም ፍርደኛው አሌክሳንደር ለመንታ ወንድሙ ጂያንካርሎ ዴልጋዶ ከሶዳ ጋር የተገናኘ ማደንዘዣ መጠጥ እንደሰጠው ተገልጿል።

ጂያንካርሎ መጠጡን ከጠጣ በኋላ ወንድሙን ለመጠየቅ በሄደበት ክፍል ራሱን ስቶ ይወድቃል፥ አሌክሳንደርም የጂያንካርሎን ልብስ አውልቆ በመልበስና ወንድሙን በተኛበት ትቶ የማረሚያ ቤቱን ግቢ ለቆ ይወጣል።

አሌክሳንደር ከወጣ በኋላም ጂያንካርሎ ከገባበት ሰመመን ይነቃል፤ በዚህ ጊዜ በፖሊሶች ተከቧል መለስ ብሎም ሁኔታውን ለፖሊሶች ለማስረዳት ቢሞክርም ሰሚ በማጣቱ በወንድሙ ክፍል እንዲገባ ተደርጓል።

ፖሊሶችም ከተደጋጋሚ ውትወታ በኋላ የጂያንካርሎን አሻራ መዝገባቸው ላይ ከሚገኘው መረጃ ጋር ያመሳክሩታል፤ ይህ ብቻውን ግን ለጥየቃ የመጣውን ወንድም ችግር መፍታት አልቻለም።

Giancarlo_Delgado.jpg

 

ጂያንካርሎ

ሁሉም የወንድምህ ግብረ አበር ነህ በማለት በእርሱ ላይ ጣታቸውን ይቀስራሉ፤ ደግነቱ ግን ወጣቱ ከወንድሙ ወንጀል ጋር በተያያዘ በወንጀል ተባባሪነት አልተከሰሰም ነበር።

በዕለቱ የነበረው የደህንነት ካሜራም አሌክሳንደር የመንትያውን ልብስ በመልበስ ስድስት የሚደርሱ መቆጣጠሪያ በሮችን ሲያልፍ አሳይቷል።

በዚህ ጊዜ ግን የመቆጣጠሪያ በር ጠባቂዎች እንደተለመደው ጠያቂዎች አሻራቸውን እንዲሰጡ አለማድረጋቸው ተጠቅሷል።

በዚህ ሳቢያም የእስር ቤቱን ዳይሬክተር ጨምሮ በርካታ ጠባቂዎች ከእስር ተባረዋል ነው የተባለው።

አሌክሳንደር ጀፈርሰን ዴልጋዶ ከማረሚያ ቤቱ ካመለጠ በኋላ ከመዲናዋ ሊማ ወጣ ብላ በምትገኝ የወደብ ከተማ ሲዝናና ቆይቷል።

ፖሊስም ግለሰቡን ለጠቆመ 20 ሺህ የፔሩ ገንዘብ ወይም 6 ሺህ 100 የአሜሪካ ዶላር ለመስጠት ቃል ቢገባም ሊገኝ አልቻለም።

አሌክሳንደር በበኩሉ እናቱን ለማየት ካለው ጉጉተ የተነሳ ከማረሚያ ቤት ማምለጡን ገልጿል።

የፔሩ ፖሊስም ከረጅም ጊዜ ክትትል በኋላ በወደቧ ከተማ በድጋሚ በቁጥጥር ስር አውሎታል፤ ቀሪ ቅጣቱን እንዲጨርስም ወደ ቻላፓልካም ማረሚያ ቤት ተዛውሯል።

ጂያንካርሎ መንትያውን እንድሚወደው ቢገልጽም ይቅርታ ለማድረግ እንደሚቸገርና በጉዳዩ ላይ ወንድሙን ማናገር እንደሚፈልግ ተናግሯል።

 

 

ምንጭ፦ ኦዲቲ ሴንትራል