ፊፋ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ወደ 48 እንዲያድግ ወሰነ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አለማቀፉ የእግር ኳስ ማህበር /ፊፋ/ በዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉ ሀገራት ቁጥር ወደ 48 እንዲያድግ ወስኗል።

ዛሬ ስዊዘርላንድ ዙሪክ የዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉ ሀገራትን ቁጥር በማሳደግ ዙሪያ ድምጽ ተሰጥቷል።

በዚህም መሰረት በ32 ቡድኖች መካከል ይደረግ የነበረው የጥሎ ማለፍ ውድድር ወደ 48 እንዲያድግ የቀረበው ሀሳብ አብላጫ ድምጽ ማግኘቱ ተነግሯል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2026 ከሚደረገው የዓለም ዋንጫ አንስቶም የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር 48 እንደሚሆን ነው የተገለጸው።

ተሳታፊ ሀገራቱ በ16 ምድብ ተከፋፍለው የጥሎ ማለፍ ውድድራቸውን የሚያደርጉ ሲሆን፥ እያንዳንዱ ምድብም ሶስት ቡድኖችን በውስጡ የያዘ ይሆናል ተብሏል።

አዲሱ የፊፋ አሰራር ከዚህ በፊት በዓለም ዋንጫ ላይ ይደረገ የነበረውን አጠቃላይ የጨዋታ መጠን ከ64 ወደ 80 እንደሚያሳድግም ነው የተገለጸው።

ከዚህ በተጨማሪም የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ማደግ ለአፍሪካና ለኢስያ አገራት የመሳተፍ እድላቸውን ያሰፋዋል ተብሏል።

የአውሮፓ ሀገራት ተሳታፊዎች ከ13 ወደ 16 ያድጋል የተባለ ሲሆን፥ በዓለም ዋንጫ ላይ በ4 እና 5 ሀገራት ብቻ የሚወከሉት የአፍሪካ እና የእሲያ ተሳታፊ ሀገራት ቁጥርን ደግሞ ወደ 9 ሊያሳድገው ይችላል።

ፊፋ አሁን ባለው አሰራር ከአንድ ዓለም ዋንጫ ላይ 521 ሚሊየን ዩሮ ትርፍ የሚያገኝ ሲሆን፥ የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ወደ 48 በሚያድግበት ጊዜ ደግሞ ትርፉ ወደ 5 ነጥብ 29 ቢሊየን ዩሮ ሊያድግ እንደሚችልም ተገምቷል።

የፊፋ ፕሬዝዳንት ጊያኒ ኢንፌንቲኖ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የተሳታፊ ሀገራትን ቁጥር አሳድጋለው ማለታቸውን ተከትሎ ዘመቻውን ሲመሩ ቆይተዋል።

በመጨረሻም የፕሬዝዳንቱ ጥረት የተሳካላቸው ሲሆን፥ በፊፋ አባል ሀገራት ዘንድ አብላጫ ድምጥ በማግኘት ሀሳባቸው ውሳኔ ላይ ሊደርስ ችሏል።

ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk/sport

 

በሙለታ መንገሻ

android_ads__.jpg