ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የወልዲያ ስታዲየም ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የወልዲያ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታዲየም እና የስፖርት ማዕከል ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ዛሬው እለት ተመርቋል።

በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሰለኝና የአማራ ክልልስ ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸወን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

haile_woldia_2.jpg

ስታዲየሙን በይፋ የመረቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፥ የስፖርት ልማቱን ለማሳደግ የግል ባለሀብቶች እና የህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በወልዲያ ከተማ ይህን የመሰለ ዘመናዊ ስታዲየም መገንባቱም የአካባቢው ማህበረሰብ ራሱን በስፖርት እንዲያዳብር ያደርጋል ሲሉም ተናግረዋል።

ስታዲየሙ በቀጣይ የአማራ ክልል ትልልቅ ውድድሮችን እንዲያስተናግድ ሰፊ እድል ይፈጥራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፥ ከዚህም ባለፈ ሀገሪቱ ትልልቅ ውድድሮችን ማዘጋጀት በምትፈልግበት ጊዜ አንድ ግብአት እንደሚሆንም ገልጸዋል።

haile_woldia.jpg

መንግስት እንዲህ አይነት ዘመናዊ ስታዲየሞችን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለማስገንባት ከግል ባለሀብቶች እና ከህብረተሰቡ ጋር አብሮ እንደሚሰራም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፥ የወልዲያ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታዲየም መጠናቀቁ በክልሉ ከፍተኛ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ስታዲየሙ ለአካባቢው ማህበረሰብ ከሚሰጠው ጥቅም ባለፈም ግንባታው 85 በመቶ ላይ የሚገኘውን የባህር ዳር ስታዲየምን ለማጠናቀቅ እና ሌሎች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለማስፋፋት ጉልህ ሚና እንዳለውም አስታውቀዋል።

ስታዲየሙን በማስገንባት ለወልዲያ ህዝብ በስጦታ መልክ ያብረከቱት ሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ፥ የወልዲያን ህዝብ ከልጅነቴ አንስቶ አውቀዋለው፤ ስፖርት ወዳድ ህዝብ ነው ብለዋል።

ይህ ስታዲየም ለወልዲያ ህዝብ ሲያንሰው ነው እንጂ አይበዛበትም ሲሉም ተናግረዋል።

በምርቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ለሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ እና ለዶክተር አረጋ ይርዳው ላደረጉት ሁሉ የከተማ አስተዳደሩና የወሎ ህዝብ የተለያዩ ሽልማቶችን አበርክቷል።

ሽልማቱን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እጅ ተቀብለዋል።

haile_woldia_3.jpg

የወልዲያ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታዲየም እና የስፖርት ማዕከል ባጠቃላይ ከ567 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን፥ ሙሉ በሙሉ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ወጪው ተሸፍኗል።

በወንበር ከ25 ሺህ 600 በላይ ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚችለው ስታዲየሙ፥ 10 የመግቢያ በሮች አሉት።

ከአስሩ የመግቢያ በሮች ስድስቱ ተመልካቾችን የሚያስገቡ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ የክብር እንግዶች፣ የተጫዋቾች እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መግቢያ መሆናቸው ታውቋል።

የስታዲየሙ በሮች በአካባቢው ባሉ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቦታዎች እንደዚሁም ስታዲየሙ እንዲገነባ ትልቅ ሚና በተጫወቱ ሰዎች ስም ነው የተሰየሙት።

የወልዲያ ስታዲየም በኢትዮጵያ ታሪክ ሙሉ በሙሉ ጣሪያ ያለው በመሆን የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

የዓለም አቀፍ አትሌቲክሶች ማህበር ደረጃን ያሟላ ባለ ስምንት መም የመሮጫ ትራክ፣ የአሎምፒክ ውድድርን የማስተናገድ አቅም ያለው መዋኛ ገንዳ፣ የቅርጫት ኳስ ሜዳ፣ የእጅ ኳስ፣ የመረብ ኳስና የቴንስ መጫዋቻዎችን ያካተተው የወልዲያ ስታዲየም ግንባታው አራት ዓመት ተኩል ወስዷል።

ከአካባቢው ማህበረሰብ በተሰበሰበ 31 ሚሊየን ብር የተገነቡ የእንግዳ ማረፊያዎችም አሉት።

የአካበቢው ማህብረሰብ የስታዲየሙን ምርቃት አስመልክቶ ከትናንት ጀምሮ ደስታውን እየገለፀ ሲሆን፥ ሙሉ በሙሉ ገንብቶ ለሰጣቸው ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከዚህ በፊት የስፖርት ማዘውተሪያዎች በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው፥ የዞኑ የተለያዩ የስፖርት እንቅስቃሴዎች ተቀዛቅዘው የነበረ ሲሆን፥ የስታዲየሙ መገንባት ለአካበቢው ማህበረሰብ ትልቅ የሆነ የስፖርት መነቃቃትን እንደሚፈጥር ነዋሪዎቹ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በአረጋ ከፈለው

 

android_ads__.jpg