የካፍ ፕሬዚዳንት አዲስ አሰራር በመዘርጋት የአፍሪካ እግር ኳስን እንደሚያሳድጉ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ)አዲስ አሰራር በመዘርጋት የአፍሪካ እግር ኳስን ለማሳደግ እንደሚሰሩ አዲሱ የካፍ ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ለተከታታይ ሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) 39ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤና 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ትናንት የካፍ ፕሬዚዳንት በመምረጥና ሌሎች ውሳኔዎች በማሳለፍ ተጠናቀቀ።

ለካፍ ፕሬዚዳንትነት የተመረጡት ማዳጋስካራዊው አህመድ አህመድ "የካፍ ፕሬዚዳንት ሆኜ የተመረጥኩት የግሌ ሀብት ለማደለብ ሳይሆን የአፍሪካ እግር ኳስን ለማሳደግ ነው" ብለዋል።

እግር ኳሱን ለማሳደግ አዲስ አሰራር እንደሚዘረጉ ነው ፕሬዚዳንቱ የገለጹት።

በተለያየ መንገድ የሚገኘውን ገቢ ግልጽ በሆነ መንገድ ለካፍ አባል አገሮች እንደሚያከፋፍሉም ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ ከካፍ አባል አገሮችና ከፊፋ ጋር ተቀራርቦ በመስራት በእግር ኳሱ ለውጥ ማምጣት እንደሚፈልጉ ነው የገለጹት።

እግር ኳስ ካለመገናኛ ብዙሃን የትም መድረስ እንደማይችል ጠቁመው፤ “ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በቅርበት እሰራለሁ” ብለዋል።

ከ29ኝ ዓመታት በኋላ የተሰናበቱት ኢሳ ሀያቱ ልምዳቸውን ለአዲሱ ፕሬዚዳንት ለማካፈል ፍቃደኝነታቸውን ገልጸዋል።

"የቀድሞ የፊፋ ፕሬዚዳንት ሴቭ ብላተር በ78 ዓመታቸው ፊፋን ሲያስተዳድሩ ምንም አልተባሉም። እኔ ግን በ70 ዓመቴ መምራት አይችልም ተብሎ መወራቱ አሳዝኖኛል" ብለዋል ኢሳ ሀያቱ።

ይህ ሊሆን የቻለው “የካፍ አባል አገሮች ስላልወደዱኝ ሳይሆን ፊፋ እኔን ስለማይፈልገኝ ነው” በማለት ነው የተናገሩት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለቀጣይ አራት ዓመታት ካፍን በስራ አስፈጻሚነት የሚያገለግሉ አባላትም ምርጫ ተካሄዷል።

ለካፍ ስራ አስፈጻሚነት ስድስት አባላት ከተለያዩ የአፍሪካ ዞኖች ተመርጠዋል።

መካከለኛ ምስራቅ በመወከል ለስራ አስፈጻሚነት የተወዳደሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻና ሱዳናዊው ማግዲ ሻምስ ኤልዲን ወደ ሁለተኛ ዙር ማለፍ ቢችሉም፤ በፈቃዳቸው ከውድድሩ ራሳቸውን አግለዋል።

ስለዚህ በመጀመሪያ ዙር 20 ድምጽ ያገኙት የጂቡቲው ሱሊማን ሀሰን ዋበሪ መካከለኛና ምስራቅ አፍሪካን በመወከል ለካፍ ስራ አስፈጻሚነት ተመርጠዋል።

ከፕሬዚዳንትና ስራ አስፈጻሚዎች ምርጫ በተጨማሪ ካፍ ለአፍሪካና ለአገራቸው እግር ኳስ ዕድገት አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላት ሽልማት አበርክቶላቸዋል።

ሽልማት ከተበረከተላቸው ጋዜጠኞች መካከል ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ከኢትዮጵያ የወርቅ ሽልማት አግኝተዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀልም ሽልማት ተቀዳጅተዋል።

ትናንት በነበረው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ዛንዚባር ቀዋሚ የካፍ አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ነበር።

ካፍም ጥያቄዋን ተቀብሎ ዛንዚባር 55ኛ ቀዋሚ የካፍ አባል መሆንዋን በይፋ አስታውቋል።

ምንጭ፦ኢዜአ