በፕሪሚየር ሊጉ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል ቀንቶታል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ19ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ተካሂደዋል።

በዚህም መሰረት 9 ስአት ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያደረጉት በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ለኢትዮ ኤሌክትሪክ የማሸነፊያዋን ብቸኛ ጎልም ፍጹም ገብረማርያም በ7ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፏል።

11 ስአት ከ30 ላይ ደግሞ በሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዷል። ሁለቱ ክለቦች 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።

ሀይሌ እሸቱ አዲስ አበባ ከተማን በ7ኛው ደቂቃ መሪ ቢያደርግም በረከት ይስሃቅ በ21ኛው ደቂቃ ድሬዳዋ ከተማን አቻ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በትናንትናው እለትም የተካሄደ ሲሆን፥ ደደቢት እና ወልዲያ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል።

ጅማ ላይ ጅማ አባቡና ከአርባምንጭ ከተማ እንዲሁም ሶዶ ላይ ወላይታ ከሲዳማ ቡና ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ ያለምንም ግብ ተጠናቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታ ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተራዝሟል።