ታላቁ ሩጫ በጁባ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ሊያካሂድ ነው።

የታላቁ ሩጫ መስራች አትሌት ሀይሌ ገብረ ስላሴ፣ በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን እና በጁባ ባለሀብት የሆኑት ኢትዮጵያዊ አቶ አይሸሹም ተካ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን በጋዜጣዊ መግለጫቸው በጁባ አሁን ያለው ሁኔታ ሰላማዊ በመሆኑ ምንም አይነት ችግር አይፈጠርም ብለዋል።

አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ ደቡብ ሱዳናውያንን እርስ በርስ ለማስተሳሰር እና የሩጫ ባህላቸውን ለማሳደግ ለመጀመሪያ ጊዜ በጁባ የሚደረገው “ታላቁ ሩጫ በጁባ” ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግሯል።

ባለሃብቱ አቶ አይሸሹም ተካ ከደቡብ ሱዳን መንግስት እና ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ውድድሩ በጁባ እንዲዘጋጅ ሀሳቡን ማቅረባቸው ተገልጿል።

በዚህም ውድድሩ መጋቢት 29 2009 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወስኗል። ከሩጫ ውድድሩ የሚገኘው ገቢም በደቡብ ሱዳን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ይውላል።

አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ እና አቶ አይሸሹም ተካ በመጪው ሀሙስ በጁባ ተመሳሳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ።

ታላቁ ሩጫ በጁባ 5 ሺህ ተሳታፊዎች እንደሚኖሩት ይጠበቃል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በጋና እና ላይቤሪያ ተመሳሳይ ውድድሮችን ማስጀመሩ ይታወቃል።

 

 

በአረጋ ከፈለው