በፕሪምየር ሊጉ አዳማና ሲዳማ ቡና ድል ቀንቷቸዋል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ጨዋያዎች ዛሬ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ተደርገዋል።

ዛሬ በ9 ሰዓት ላይ በተደረጉ ጨዋታዎችም ፋሲል ከነማ በሜዳው አዲስ አበባ ከተማን ያስተናደገ ሲሆን፥ ጨዋታውን በአዲስ አበባ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በጨዋታው ላይም ሀይሌ እሸቱ በ61ኛው ደቂቃ ለአዲስ አበባ ከተማ የማሸነፊያ ጎሉን ከመረብ አሳርፏል።

ወላይታ ድቻ በሜዳው ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደ ሲሆን፥ ጨዋታውም በባለሜዳው ወላይታ ድቻ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የወላይታ ድቻው አብዱልሰመድ አሊ በ45ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻን የማሸነፊያ ጎል በማስቆጠር ክለቡ በሜዳው ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሏል።

ሲዳማ ቡና ከጅማ አባቡና ጋር ያደረጉት ጨዋታም በሲዳማ ቡና 1ለ0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን፥ ሲዳማ ቡና በሜዳው ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት ችሏል።

በጨዋታው ላይ ፀጋዬ ባልቻ ለሲዳማ ቡና መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ለመጠናቀቅ ሶስት ደቂቃ ሲቀሩ በ87ኛው ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል።

9 ሰዓት ላይ የተደረገ ሌላ ጨዋታ አዳማ ላይ አዳማ ከተማን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አገናኝቷል።

ጨዋታውም በአዳማ ከተማ 2ለ0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን፥ አዲስ ህንፃ በ72ኛው ደቂቃ እንዲሁም ቡልቻ ሹራ በ52ኛው ደቂቃ የአዳማን የማሸነፊያ ጎሎች ከመረብ አሳርፈዋል።

ደደቢት ከአርባ ምንጭ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ 2ለ2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

 

በሙለታ መንገሻ