በዩሮፓ ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ አንደርሌክትን በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ትናንት ምሽት የዩሮፓ ሊግ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታዎች ተካሂደዋል፡፡

በኦልድትራፎርድ አንደርሌክትን ያስተናገደው ማንቼስተር ዩናይትድም 2 ለ 1 አሸንፏል፡፡

ለቀያዮቹ ሰይጣኖች ሚኪታሪያን በ10ኛው ደቂቃ መሪ የሚያደርጋቸውን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ሆኖም የአንደርሌክቱ ሃኒ በ32ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ሁለቱ ቡድኖች መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜውን 1 ለ 1 እንዲያጠናቅቁ አስገድዷቸዋል።

ከ90 ደቂቃው ውጭ በተጨመረ የ30 ደቂቃ ጨዋታ ላይ ማርከስ ራሽፎርድ 107ኛው ደቂቃ ላይ ለዩናይትድ የማሸነፊያዋን ጎል ከመረብ አዋህዷል፡፡

በዚህም ማንቼስተር ዩናይትድ በደርሶ መልስ ድምር ውጤት 3 ለ 2 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

በሌሎች ጨዋታዎች ሊዮን እና ቤሺክታሽ በተገናኙበት ግጥሚያ በ120 ደቂቃ ጨዋታ ቤሺክታሽ 2 ለ 1 አሸንፏል፡፡

በደርሶ መልስ ድምር ውጤት ሁለቱ ቡድኖች 3 ለ 3 በመለያየታቸው ወደ መለያ ምት አምርተው፥ ሊዮን 7 ለ 6 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜ መግባቱን አረጋግጧል።

የጀርመኑ ሻልከ 04 ከአያክስ አምስተርዳም ያደረጉት ጨዋታ ለሆላንዱ ክለብ መልካም ሆኖ አልፏል።

በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሻልከ 2 ለ 0 መምራት ችሏል፤ በመጀመሪያው ጨዋታ አያክስ 2 ለ 0 በማሸነፉ ጨዋታው ወደ ጭማሪ ሰዓት አምርቷል።

በጭማሪ ሰዓቱም ሻልከ አንድ ጎል ሲያስቆጥር አያክስ ደግሞ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠሩ፥ ሻልከ 3 ለ 2 ቢያሸነፍም አያክስ በደርሶ መልስ ድምር ውጤት 4 ለ 3 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜ ገብቷል፡፡

የቤልጅየሙ ጌንክ በሜዳው የስፔኑን ሴልታቪጎ ያስተናገደበት ጨዋታ ደግሞ 1 ለ 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በደርሶ መልስ ድምር ውጤትም ሴልታቪጎ 4 ለ 3 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፏል።

ዛሬ በስዊዘርላንዷ ኒዮን የቻምፒየንስ ሊግ እና ዩሮፓ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ድልድል 8 ሰዓት ላይ ይፋ ይሆናል።