ግማሽ ፍጻሜው የማድሪድ ደርቢን ያስተናግዳል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 13 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ድልድል ዛሬ በኒዮን ስዊዘርላንድ ወጥቷል።

በድልድሉ ሁለቱ የማድሪድ ከተማ ክለቦች ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ተገናኝተዋል።

ሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ደግሞ ጁቬንቱስን ከሞናኮ አገናኝቷል።

በማድሪዱ ደርቢ የአውሮፓ ምሽት ሪያል ማድሪዶች የተሻለ ታሪክ ባለቤት ናቸው።

ሁለት ጊዜ በፍጻሜ ተገናኝተው ሪያል ማድሪድ በጨዋታ እና በመለያ ምት የዋንጫ ባለቤት መሆኑ ይታወሳል።

ሁለቱ ክለቦች ለዘንድሮው የካርዲፉ የፍጻሜ ፍልሚያ ለመድረስም ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ።

በሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ጁቬንቱስ ከሞናኮ ይጫወታሉ።

በዘንድሮው የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ጠንካራ ተከላካይ እና ጠንካራ አጥቂን የያዙት ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታም ይሆናል።

ግማሽ ፍጻሜው የመጀመሪያ ጨዋታዎችም በያዝነው ወር የመጨረሻ ሳምንት ይደረጋሉ።

በሌላ በኩል በዩሮፓ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ድልድልም ይፋ ሆኗል።

የእንግሊዙ ማንቼስተር ዩናይትድ ከስፔኑ ሴልታቪጎ ሲጫወት አያክስ ከሊዮን ይገናኛል።

ማንቼስተር የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጭ በማድረግ በሳምንቱ ለፍሬንድስ አሬናው የፍጻሜ ፍልሚያ በኦልድትራፎርድ የስፔኑን ተወካይ ያስተናግዳል።

የሆላንዱ አያክስ የመጀመሪያ ጨዋታውን በሜዳው ካከናወነ በኋላ ለመልሱ ጨዋታ ወደ ፈረንሳይ ያቀናል።

የግማሽ ፍጻሜው የመጀመሪያ ጨዋታ በፈረንጆቹ ግንቦት 4 ከተከናወነ በኋላ በሳምንቱ የመልስ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።