ፌደሬሽኑ ለአትሌቲክስ ስፖርት ብቁ አትሌቶች ማግኘት ይቻላል ተብሎ የታመነባቸውን አካባቢዎች ለየ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ለአትሌቲክስ ስፖርት "ብቁ አትሌቶች ማግኘት ይቻላል" ተብሎ የታመነባቸውን "የተስጦ አካባቢዎች" ለየ።

ፌደሬሽኑ አካባቢዎችን የለየው በአገር አቀፍ ደረጃ ባካሄደው ምልከታ ነው።

ምልከታውን አስመልክቶ ከክለቦች፣ ከማሰልጠኛ ማዕከላት እንዲሁም ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር ትናንት ውይይት አድርጓል።

የፌደሬሽኑ የጥናት፣ ምርምርና ስልጠና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ብርሃኑ እንደገለጹት፥ የተስጦ አካባቢዎቹ የተለዩት ከጥር አጋማሽ ጀምሮ ሲካሄድ በቆየ ምልከታ ታግዞ ነው።

የአካባቢው ከፍታ፣ ከዚህ ቀደም ውጤታማ የሆኑ አትሌቶች የፈሩባቸው ቦታዎች፣ አመጋገብ፣ ባህል መሰረት ተደርጎ አካባቢዎቹ መለየታቸውን ገልጸዋል።

በዚህ መሰረት በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሽዋ፣ ጉጂ ዞን፣ አሰላና በቆጂ መካከለኛና ረጅም ርቀት፤ በሻምቡ፣ በሆሮ ጉዱሩ የረጅም ርቀት፤ በነቀምት ዶዶላ፣ በሻምቡና በቆጂ አጭርና የሜዳ ላይ ተግባራት(ዝላይና ውርወራ) ይገኛሉ ተብሏል።

በአማራ ክልል በቲሊሊ የመካከለኛ፣ የረጅም ርቀት፣ የርዝመትና ከፍታ ዝላይ፤ በደንበጫ የሜዳ ላይ ተግባራት የሚገኙባቸው ቦታዎች መሆናቸውን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።

በደቡብ ክልል በአርቢጎና፣ በሜሻ፣ በኢሊቶ ውሪሮ፣ በጉራጌ የመካከለኛና የረጅም ርቀት፤ በጂንካ፣ በአርባ ምንጭ፣ በኮንሶ የአጭርና የሜዳ ላይ ተግባራት ውጤታማ አትሌቶች እንደሚገኙ ተመልከቷል።

በትግራይ ክልል በእንዳመሆኒና በአላጄ የረጅም ርቀት ሯጮች፤ በመቕሌ፣ በዕዳጋ ዓርቢና በውቅሮ የአጭርና የመካከለኛ ርቀት ሯጮች የተሰጦ አካባቢ ተደርገው ተለይተዋል።

በጋምቤላ ክልል በአጭር ርቀትና የሜዳ ላይ ተግባራት፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ የአጭር፣ የመካከለኛ፣ የውርወራና ዝላይ አትሌቶች እንደሚገኙ ታምኗል።

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የመካከለኛ ርቀት እና የከፍታ ዝላይ፤ በአፋር ክልል የአጭር፣ መካከለኛና ረጅም ርቀት፤ በድሬዳዋ የእርምጃና አጭር ርቀት፣ በሐረር ክልል የመካከለኛና ረጅም ርቀት አካባቢዎች ተብሎ የተለዩ ናቸው።

በአገር አቀፍ ደረጃ የተመረጡ የተስጥኦ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ተዳስሰዋል ማለት እንዳልሆነ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በቀጣይም ቦታዎችን የመለየት ስራ እንደሚሰራ ነው አቶ ሳሙኤል የገለጹት።

ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው በምልከታ የተለዩ የተስጥኦ አካባቢዎች ላይ አትሌቶችን ለመመልመል በጀት መድበው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር እንዲገቡ ጠይቀዋል።

ሌሎች ያልተዳሰሱ ቦታዎች በስፋት መዳሰስ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

በባለድርሻ አካላት የተሰጡ ግብአቶች ተካትተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ እንደሚገባም ፌደሬሽኑ አስታውቋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ