ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ የሚገኘውን አዲስ አበባ ከተማ አሸንፏል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) 28ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሲጀመር ኢትዮጵያ ቡና ድል ቀንቶታል።

ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ የሚገኘውን አዲስ አበባ ከተማ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ነው ያሸነፈው።

አበቡበከር ነስሩ እና ሳሙኤል ሳኑሚ የማሸነፊያ ግቦቹን በመጀመሪያው አጋማሽ አስቆጥረዋል።

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና በእኩል 47 ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።  

በነገው እለትም ሊጉ ሲቀጥል ሰባት ጨዋታዎች በተመሳሳይ 9 ስአት ላይ ይደረጋሉ።

በዚህም መሰረት የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮ ኤሌክትሪክን ይገጥማል። የሊጉ ሻምፒዮን ለመሆን አራት ነጥቦች ብቻ መሰብሰብ የሚጠበቅበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮ ኤሌክትሪክን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ፋሲል ከተማ ከመከላከያ፣ ወልድያ ከጅማ አባ ቡና፣ ሲዳማ ቡና ከአርባምንጭ ከተማ፣ አዳማ ከተማ ከደደቢት እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ ነገ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ግንቦት 4 ሊደረጉ የነበሩ የ28ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ወደ ግንቦት 10 2009 ዓ.ም እንዲተላለፉ መወሰኑ ይታወሳል።

በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን የምድብ ጨዋታ ከደቡብ አፍሪካው ማሚሎዶ ሰንዳውስ ጋር ጨዋታ ማድረጉ እንዲሁም በክለቦች መካከል ከፕሪሚየር ሊጉ ላለመውረድ እርስ በእርስ ሲገናኙ ሆን ብሎ ነጥብ የመልቀቅ አዝማሚያ ስለተስተዋለ መርሃ ግብሮቹ ወደ ግንቦት 10 መዘዋወራቸውን ፌዴሬሽኑ ማሳወቁ አይዘነጋም።

ፕሪሚየር ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ52 ነጥብ ሲመራ፤ ደደቢት በ48፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡና በእኩል 47 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

ድሬዳዋ ከተማ በ28 ነጥብ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ25 እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ በ20 ነጥብ በሊጉ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

ኮከብ ግብ አግቢነቱን ደግሞ ጌታነህ ከበደ በ21 ጎሎች ይመራዋል፤ ሳላዲን ሰይድ በ15፣ ጃኮ አራፋት በ12፣ ፍፁም ገብረማርያም እና አዳነ ግርማ በእኩል 11 ግቦች ይከተላሉ።

 

 

 

በፋሲካው ታደሰ