በዓለም ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 5ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀቀች

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኬንያ ናይሮቢ ሲካሄድ የቆየው 10ኛው የዓለም ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት ማምሻውን ፍጻሜውን አግኝቷል።

በውድድሩ ላይ ተሳታፊ የነበረችው ኢትዮጵያም ከዓለም 5ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች።

ኢትዮጵያ አራት የወርቅ፣ ሶስት የብርና አምስት የነሃስ በድምሩ 12 ሜዳልያዎችን በማግኘት ነው ውድድሩን አምስተኛ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቀችው።

በትናንትናው እለት አትሌት መለሰ ንብረት በወንዶች 800 ሜትር፤ አትሌት ሰለሞን በርጋ በ3 ሺህ ሜትር ወንዶች የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝተዋል።
አትሌት ለምለም ሀይሉም በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች ወርቅ አስገኝታለች።

በውድድሩ መክፈቻ ኢትዮጵያ በ3 ሺህ ሜትር ሴቶች የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በአትሌት አበራሽ ምሰዎ አማካኝነት ማግኘቷ የሚታወስ ነው።

አትሌት ቶለሳ ቦደና በ800 ሜትር ወንዶች፣ አትሌት አበበ ዲሳሳ በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች እንዲሁም አትሌት ስንዱ ግርማ በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች የብር ሜዳሊያ አግኝተዋል።

የነሃስ ሜዳሊያውን ደግሞ አትሌት በለጠ መኮንን፣ አለሙ ቂጤሳ፣ ሂሩት መሸሻ፣ ይታይሽ መኮንን እና እታለማው ስንታየሁ አስገኝተዋል።

በዓለም ታዳጊዎች የአትሌቲክስ ታሪክ ኢትዮጵያ በዘንድሮው ውድድር ያገኘችው ወርቅና አጠቃላይ ሜዳሊያ ብዛት ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበበት ነው።

ውድድሩን ደቡብ አፍሪካ በ5 የወርቅ፣ በ3 የብር እና በ3 የነሃስ በድምሩ በ11 ሜዳሊያዎች በአንደኝነት አጠናቃለች።

ቻይና በ5 የወርቅ፣ በ2 የብር እና በ2 የነሃስ በድምሩ በ11 ሜዳሊያዎች 2ኛ፣ ኩባ በ5 ወርቅ፣ በ2 ብር እና በ1 የነሃስ በ8 ሜዳሊያዎች 3ኛ ስትሆን አዘጋጇ ኬንያ በ4 ወርቅ፣ በ7 ብር እና በ4 የነሃስ በድምሩ በ15 ሜዳሊያዎች 4ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።

በ10ኛው የዓለም ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና 131 ሀገራት ተሳትፈዋል።

በውድድሩ ላይ 25 ሀገራት በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ የገቡ ሲሆን፥ 15 ሀገራት ብቻ ወርቅ ተከፋፍለዋል።

በ10ኛው የዓለም ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድንም ዛሬ አዲስ አበባ መግባቱን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

በሙለታ መንገሻ