በሴቶች 5 ሺህ ሜትር የማጣሪያ ውድድር አልማዝ፣ ሰንበሬና ለተሰንበት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2009 (ኤፍ ቢሲ) በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ምሽት ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የሴቶች 5 ሺህ ሜትር የማጣሪያ ውድድር ተደርጓል።

ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ30 ጀምሮ በተካሄደው ውድድር በመጀመሪያው ምድብ አልማዝ አያና ሁለተኛ ሰንበሬ ተፈሪ ሶስተኛ በመውጣት ለፍጻሜ ሲያልፉ ኬንያዊቷ ሄለን ኦንሳንዶ ኦቢሪ አንደኛ ወጥታለች፡፡

በሁለተኛው ምድብ የተሳተፈችው ለተሰንበት ግደይ ደግሞ ከምድቧ አንደኛ በመውጣት ለፍፃሜ አልፋለች፡፡

ማምሻውን በተካሄደ የሴቶች 800 ሜትር የማጣሪያ ውድድር ሀብታም አለሙ ከምድቧ ሁለተኛ በመውጣት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች።

በዚህ የማጣሪያ ውድድር ላይ የተወዳደሩት ማህሌት ሙሉጌታ እና ኮሬ ቶላ ሳያልፉ ቀርተዋል።

ቀጥሎ የወንዶች 1 ሺህ 500 ሜትር የማጣሪያ ውድድር የተካሄደ ሲሆን፥ በውድድሩ የተሳተፈው ሳሙኤል ተፈራ እና ውድድሩን ያቋረጠው ታሬሳ ቶሎሳ ወደ ቀጣዩ ዙር ሳያልፉ ቀርተዋል።

በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ አንድ የወርቅና ሁለት የብር ሜዳልያዎችን አግኝታለች።