የኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ሊጎች ላይ ለሚወዳደሩ የክልሉ የእግር ኳስ ክለቦች የ25 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ነሐሴ 5፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ክልሉን ወክለው በተለያዩ ሊጎች ላይ ለሚወዳደሩ የእግር ኳስ ክለቦች የ25 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ።

የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ እንዳስታወቀው የገንዘብ ድጋፉ ፕሪሚየር ሊግን ጨምሮ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ሊጎች ለሚወዳደሩ ክለቦች የተደረገ ነው።

በዚህም በ2009 የከፍተኛ ሊግ አሸናፊ በመሆን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለተቀላቀለው ጅማ ከተማ የእግር ኳስ ክለብ የ10 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል።

ገንዘቡም ለተጫዋች ግዢ እና ለክለቡ ማጠናከሪያ እንደሚውል ነው ቢሮው ያስታወቀው።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተወዳዳሪ ለሆነው እና የ2009 ውድድርን 3ኛ በመሆን ላጠናቀቀው አዳማ ከተማ ደግሞ የ2 ሚሊየን ብር የገንዘብ ሽልማት መበርከቱም ተገልጿል።

ቀሪው ገንዘብ ክልሉን ወክለው በከፍተኛ ሊግ ውስጥ ለሚወዳደሩ የእግር ኳስ ክለቦች ማጠናከሪያነት የሚውል መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል።