በሴቶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል የፍጻሜ ውድድር እቴነሽ ዲሮ በሜዳሊያ ዝርዝር ውስጥ አልገባችም

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በለንደን አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ስምንተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።

በዛሬው እለትም የሴቶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል የፍጻሜ ውድድር ምሽት 5 ሰዓት ከ25 ደቂቃ ላይ ተካሂዷል።

በዛሬው ውድድር ላይ ማጣሪያውን ካለፉት አትሌት እቴነሽ ዲሮ እና ብርቱካን ፈንቴ መካከል በውድድሩ ላይ የተካፈለችው አትሌት እቴነሽ ናት።

በፍፃሜ ውድድሩ ኢትዮጵያን ወክላ የሮጠችው እቴነሽ ዲሮ በሜዳሊያ ዝርዝር ውስጥ አልገባችም።

እቴነሽ ውድድሩን 7ኛ ሆና ያጠናቀቀች ሲሆን፥ የወርቅና የብር ሜዳሊያ ወደ አሜሪካ ሲሄድ የነሃስ ሜዳሊያ የኬንያ ሆኗል።

በሻምፒዮናው ትናንት ምሽት ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የሴቶች 5 ሺህ ሜትር የማጣሪያ ውድድር መደረጉ ይታወሳል።

በውድድሩ ላይም በመጀመሪያው ምድብ አልማዝ አያና ሁለተኛ ሰንበሬ ተፈሪ ሶስተኛ በመውጣት ለፍጻሜ ሲያልፉ፥ በሁለተኛው ምድብ የተሳተፈችው ለተሰንበት ግደይ ደግሞ ከምድቧ አንደኛ በመውጣት ለፍፃሜ አልፋለች፡፡

በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ አንድ የወርቅና ሁለት የብር ሜዳልያዎችን አግኝታለች።