የግሸን ፋርማሲ በስፖርት የተከለከለ መድኃኒት ህጋዊ ባልሆነ መልኩ መሸጡ በመረጋገጡ ለ3 ወራት አገልግሎት እንዳይሰጥ ታገደ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የግሸን ፋርማሲ በስፖርት የተከለከለ መድኃኒት ህጋዊ ባልሆነ መልኩ መሸጡ ስለተረጋገጠ ለሶስት ወራት አገልግሎት እንዳይሰጥ መታገዱን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ቀደም ሲል በፈረንጆቹ ነሐሴ 4 ቀን 2017 ከስፖርት አበረታች ቅመሞች በተያያዘ በመድሃኒት ቤቱ ላይ የምርመራ ዘገባ ማውጣቱ ይታወቃል።

አለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ ባወጣው የተከለከሉ መድኃኒቶችና ዘዴዎች ዝርዝር ውስጥ በቀዳሚነት የተካተተው፥ “EPO” ወይም በሳይንሳዊ ስያሜው “Erythropoietin” የተባለው መድኃኒት፥ ስታዲየም አካባቢ በሚገኘው የግሸን ፋርማሲ ያለምንም የሐኪም ትዕዛዝ በቀላሉ እንደሚሸጥና ስፖርተኞችም በቀላሉ እየገዙ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ጋዜጣው ማስነበቡ ይታወሳል።

ጋዜጣው ሀገሪቱ በአለም አቀፍ የውድድር መድረኮች የገነባችውን መልካም ገፅታ ለማስቀጠል በየደረጃው እያካሄደች ያለውን ዘርፈ-ብዙ ጥረት በሚዛኑ ያላስቀመጠ መሆኑን ሚኒስቴሩ በመግለጫው ጠቅሷል።

አንድን ፋርማሲ ብቻ በናሙናነት በመውሰድ ኢትዮጵያ ውስጥ የዶፒንግ ምርቶችን በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል የሚያሳይና ስፖርተኞችም እየገዙ ይጠቀማሉ በማለት ጋዜጣው ድምዳሜ ላይ መድረሱ ስህተት ነው ብሏል።

ሚኒስቴሩ በምርመራ ዘገባው ላይ የቀረቡትን መረጃዎች መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅህፈት ቤትና በፌዴራል እና በአዲስ አበባ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣናት የማጣራት ስራ መካሄዱን አስታውቋል።

በዚህም መድኃኒቱ በጋዜጣው ላይ በተጠቀሰው የግሸን ፋርማሲ ውስጥ እንደሚገኝ በፍተሻ መረጋገጡን ገልጾ፥ የዘጋርዲያን ጋዜጠኞች በላኩት ደረሰኝ መሰረት መድኃኒቱን ከፋርማሲው መግዛታቸውን ማወቅ መቻሉን ጠቅሷል።

ከዚህም ባሻገር በጋዜጣው ላይ ፎቶግራፋቸው የታተሙ መድኃኒቶችን መለያ ቁጥር በመመርመር ፋርማሲው በደረሰኝ ያስገባቸውን መድኃኒቶች ያለሐኪም ትዕዛዝ መሸጡ ተረጋግጧል ብሏል።

ይህን መነሻ በማድርግም ፋርማሲው ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ስታዲየም የሚገኘው የግሸን ፋርማሲ ለሶስት ተከታታይ ወራት እንዲዘጋና አገልግሎት እንዳይሰጥ ቅጣት ተጥሎበታል።

በተጨማሪም የቅርንጫፍ መድኃኒት ቤት ኃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ይበልጣል አድማሱ የሙያ ግዴታቸውንና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ በመሆኑ፥ የሙያ ፈቃዳቸው ለስድስት ወራት እንዲታገድና ፈቃዳቸውንም ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እንዲመልሱ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል ነው ያለው።

 

 

 

 


በምህረት አንዱዓለም