ዌስትሃም ዴቪድ ሞየስን አዲስ አሰልጣኝ አድርጎ ሾመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ዌስትሃም ዩናይትድ ዋና አሰልጣኝ ስላቫን ቢሊችን ከሃላፊነት ማንሳቱን ተከትሎ በምትኩ አሰልጣኝ ዴቪድ ሞየስን መሾሙን አስታወቀ።

ዴቪድ ሞየስ በዌስትሃም አሁን ያሉትን ችግሮች ለማስተካከል እና መልካም ነገሮችን ለማምጣት በትጋት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የቀድሞው የኤቨርተን እና የማንቼስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ የነበሩት ዴቪድ ሞየስ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙትን መዶሻዎቹን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማምጣት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

ሞየስ ካሳለፍነው ግንቦት ወር ወዲህ ሰንደርላንድ ወደ ቻምፒዮንሺፕ መውረዱን ተከትሎ፥ በአሰልጣኝነት ስራቸው ላይ አልነበነሩም።

የዌስትሃም ሊቀመንበር ዴቪድ ሱሊቫን የ54 ዓመቱ ስኮትላንዳዊ አሰልጣኝ፥ ክለባችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማምጣት ትክክልኛው ሰው ሲሉ ሞየስን ገልፀዋቸዋል።

በፕሪሚየርሊጉ ልምድ እና እውቀት ያለው አሰልጣኝ ያስፈልግን ነበር፤ ዴቪድ ሞየስም በዚህ በኩል ፍላጎታችንን አሟልተውታል፤ ከተጫዋቾቻችን ጋር ሆነውም የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኙ ተስፋ አለን ነው ያሉት።

ሞየስ በዌስትሃም አሰልጣኝነት የመጀመሪያውን ጨዋታቸውን በቀጣይ በፕሪሚየር ሊጉ ከዋትፎርድ ጋር በሚደረግ ጨዋታ ይጀምራሉ።

አሰልጣኙ ላለፉት ዓመታት አምስት ክለቦችን መምራታቸውን ገልፀው፥ የአሰልጣኝነት ስራቸውን ከ20 ዓመት በፊት በፕሬስተን መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።

በፕሪሚየር ሊጉ ኤቨርተንን፣ ማንቼስተር ዩናይትድን እና ሰንደርላንድንም አሰልጥነዋል።

ከፕሪሚየር ሊጉ ውጭ ደግሞ በስፔን ላሊጋ የሪያል ሶሲዳድ አሰልጣኝ ነበሩ።

ዌስትሃም ዩናይትድ የውጤት ቀውስ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ነው ትናንት አሰልጣኝን ስላቫን ቢሊችን ከስራ ያሰናበተው።

ክለቡ በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ክለቡም ያሰበውን እቅድ ለማሳካትና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በሚል አሰልጣኙን ማሰናበቱን ይፋ አድርጓል።

ክሮሺያዊው አሰልጣኝ ቢሊች በለንደኑ ክለብ ለሁለት ዓመት ከ6 ወራት ቆይታ አድርገዋል።

ባለፈው ዓመት ክለቡ በእርሳቸው አመራር 11ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

መዶሻዎቹ ባለፈው መስከረም ወር ስዋንሲ ሲቲን ካሸነፉ ወዲህ ውጤት ርቆባቸዋል።

በሳምንቱ መጨረሻም በመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል የ4ለ1 ሽንፈትን አስተናግደዋል።

ኮትላንዳዊው አሰልጣኝ ዴቪድ ሞየስም ቢሊችን ተክተው ዌስትሃምን ተረክበዋል።

የአሁኑ የስላቫን ቢሊች ስንብት በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ አራተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።

ፍራንክ ዲቦር ከክሪስታል ፓላስ፣ ክሬግ ሼክስፒር ከሌሲስተር ሲቲ እንዲሁም ሮናልድ ኪዩመን ከኤቨርተን ቀደም ብለው የተሰናበቱ አሰልጣኞች ናቸው።

 

 

 

ምንጭ፦ቢቢሲ