በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ የኤሌክትሮኒክ ማስታወቂያዎች መታየት ሊጀምሩ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የኤሌክትሮኒክ ማስታወቂያዎችን በአዲስ አበባ ስታዲየም ላይ መጠቀም ሊጀምር ነው።

ፌደሬሽኑ በስታዲየም ሜዳ ዙሪያ ካሉ የባነር ቢል ቦርድ ማስታወቂያዎች በዓመት 4 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ያገኛል።

ይሁን እንጂ አሁን ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ አንጻር በስታዲየም ሜዳ ዙሪያ ካሉ የባነር ማስታወቂያዎች በተጨማሪ፥ የኤልክትሮኒክ ማስተወቂያዎችን መልቀቅ የሚያስችል ቴክኖሎጂን መጠቀም ሊጀመር መሆኑን ገልጿል።

ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ለማድረግ ኮሎሲኦ ከተባለው የስሎቫኪያ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር ስምምነት መፈጸሙንና፥ ቴክኖሎጂው በተያዘው ዓመት ተግባራዊ እንደሚሆን የፌደሬሽኑ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ታፈሰ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎችን ለሚያቀርብለትና ለሚገጣጥምለት ኩባንያ 9 ሚሊየን ብር ይከፍላል፡፡

ኩባንያው ቴክኖሎጂውን ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች እስከሚረከቡት፥ በራሱ ባለሙያ ስራው እንደሚጀመርም ታውቋል፡፡

እንደ አቶ ኢሳያስ ገለጻ ቴክኖሎጂው በአውሮፓ እግር ኳስ ሜዳዎች ላይ የሚታየው ዓይነት መሳሪያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ ተገጥሞ፥ የተለያዩ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ ያስችላል።

ይህም ፌደሬሽኑ በየዓመቱ አሁን ከሚያገኘው የማስታወቂያ ገቢ ከእጥፍ በላይ ማገኘት ያስችለዋል ብለዋል።

ለሀገሪቱ አዲስ የሆነውን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ፌደሬሽኑን በማማከር ስራ የተሳተፉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢንፎርሜሽን ሳይንስ መምህር ዶክተር ወንደሰን ሙሉጌታ፥ አገልግሎቱ በአንድ ጨዋታ በርካታ ማስተወቂያዎችን መልቀቅ ያስችላል ብለዋል።

ቴክኖሎጂው ገቢ ከማስገኘት በተጨማሪ ፌደሬሽኑ ለስፖርት ቤተሰቡ የተለያዩ መልዕክቶችን፣ ውሳኔዎችንና ሌሎች ስፖርታዊ ጉዳዮችን ማስተላለፍ ያስችለዋልም ብለዋል።

 

 

 

ምንጭ፦ኢዜአ