የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንትና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ምርጫ ተራዘመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ምርጫ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ወስኗል።

ፌደሬሽኑ ባዘጋጀው የጉባኤ መርሀ ግብር መሰረት ተጠባቂው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ እና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ነገ ህዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም ከ3 ሰዓት ጀምሮ እንደሚያከናወን ቢያሳይም፥ ጠቅላላ ጉባኤው  ምርጫው በሌላ ጊዜ እንዲካሄድ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል::

የኦሮሚያ ክልል እግር ኳስ ፌደሬሽን ምርጫው በአንድ ወር እንዲራዘም በይፋ መጠየቁ ይታወቃል።

ሌሎች አንዳንድ ክልሎችም ምርጫው እንዲራዘም ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልፁ ነበር::

የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ (ፊፋ) ልኳቸዋል ስለተባሉት ደብዳቤዎች እና በፌደሬሽኑ አመራሮች ወደ ፊፋ ስለተላኩት የተለያዩ ደብዳቤዎች የሚሰጠው ምላሽ እየተጠበቀ ነው::

የጉባኤው መርሃ ግብር እንደሚያሳየው የ2009 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2010 እቅዶች ለተሳታፊዎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት በመርሃ ግብሩ የወጣው መረጃ ያሳያል።

 

 

 

በመኮንን ኃይሉ