ጣሊያን ከ60 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ሳታልፍ ቀረች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጣሊያን ከ60 ዓመታት ወዲህ በሩሲያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የ2018 የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ አለማለፏን አረጋግጣለች።

ጣሊያን የትናንቱን ጨዋታ በሚላን ከስዊድን ጋር አድርጋ 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በዚህም በመጀመሪያው ዙር ከሜዳዋ ውጭ በስዊዲን የደረሰባትን የ1ለ0 ሽንፈት በማስተናገዷ ከ60 ዓመታት በኋላ ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው የእግር ኳስ ውድድር ተሳታፊ ሳትሆን ቀርታለች።

አንጋፋው የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ጂያንሉጅ ቡፎን ከጨዋታው በኋላ በእንባ ታጅቦ ሀገሩ ለዓለም ዋንጫ ባለማለፏ ማዘኑን ተናግሯል።

ጣሊያን የዓለም ዋንጫን አራት ጊዜ ያነሳች ሲሆን፥ ዘንድሮ ከዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ውጭ ስትሆን ከፈረንጆቹ 1958 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽትም ይደረጋሉ።

በአሰልጣኝ ማርቲን ኦ ኒዬል የምትመራው ሪፐብሊክ ኦፍ አየርላንድ በአቪቫ ስታድየም ዴንማርክን ታስተናግዳለች።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ኮፐን ሃገን ላይ የተደረገውን ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።

ከሮቢ ኪን በኋላ ወሳኝ አጥቂ አላገኘም የሚባለው የአየርላንድ ብሔራዊ ቡድን እየተከተለ ባለው መከላከልን መሰረት ያደረገ ጨዋታ ከፍተኛ ትችት ቢያስተናግድም፥ ምሽት 4 ሰዓት ከ45 የሚደረገውን ጨዋታ በአሸናፊነት ለመወጣት ብቃት አለው ሲሉ አሰልጣኙ ኦ ኒዬል ተናግረዋል።

በአሰልጣኝ ክሪስ ኮልማን የምትመራው ዴንማርክ በበኩሏ ግብ የተቆጠረበት የአቻ ውጤት ስለሚያሳልፋት የተሻለ የማለፍ እድልን ይዛ ወደ ዱብሊን አምርታለች።

አውስትራሊያ ከሆንዱራስ እና ፔሩ ከኒውዚላንድ በቀጣይ በሚያደርጉት የመጨረሻ ጨዋታም የመጨረሻዎቹ 32 የዓለም ዋንጫው ተሳታፊዎች ይለያሉ።

 

 

 

 

በምንተስኖት መለሰ