ዌስትብሮምዊች አልቢዮን አሰልጣኝ ቶኒ ፑሊስን አሰናበተ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 11 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የእንግሊዙ ዌስትብሮምዊች አልቢዮን አሰልጣኝ ቶኒ ፑሊስን ማሰናበቱን አስታወቀ።

ዌስትብሮሞች የመጀመሪያ ሶስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችለው ነበር።

ይሁን እንጅ ከዚያ ወዲህ ባሉት ጨዋታዎች ሽንፈትና አቻ በማስተናገድ ከወራጅ ቀጠና በአንድ ነጥብ ርቀው ተቀምጠዋል።

በፕሪሚየር ሊግም ሆነ ካራባኦ ካፕ (የቀድሞው ሊግ ካፕ) ቡድኑ ካሸነፈ 10 ጨዋታዎች ተቆጥረዋል።

በሳምንቱ መጨረሻም በሜዳቸው በቼልሲ 4 ለ 0 ሽንፈት አስተናግደዋል።

በቀጣይ ውጤታማ ጉዞ ለማድረግና ክለቡ ከገባበት የውጤት ቀውስ ለመውጣት የክለቡ ቦርድ አሰልጣኙን ማሰናበቱን ይፋ አድርጓል።

ለጊዜው የእርሳቸው ምክትል የነበሩት ጋሪ ማግሰን ቀጣዩ አሰልጣኝ በይፋ እስከሚታወቅ ድረስ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆነዋል።

ቶኒ ፑሊስ በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛው ተሰናባች አሰልጣኝ ሆነዋል።

ከእርሳቸው ቀደም ብሎ ፍራንክ ዲቦር፣ ክሬግ ሼክስፒር፣ ሮናልድ ኪዩመን እና ስላቫን ቢሊች የተሰናበቱ አሰልጣኞች ናቸው።