ሩሲያ ከ2018ቱ የክረምት ኦሊምፒክ ታገደች

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 27 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) አለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሩሲያን ከ2018ቱ የክረምት ኦሊምፒክ አገደ።

የአለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባህ ውሳኔውን ትናንት በስዊዘርላንድ ሉዛን ይፋ አድርገዋል።

የሩሲያ ድርጊት የተቋሙንም ሆነ የየትኛውንም የስፖርት ደንብ የሚጻረር በመሆኑ ውሳኔው መተላለፉንም ገልጸዋል።

በ2014 በሩሲያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የሶቺ የክረምት ኦሊምፒክ ላይ፥ በመንግስት የሚደገፍ አበረታች መድሃኒት ጥቅም ላይ ውሏል የሚል ወቀሳ ከቀረበ በኋላ ኮሚቴው ጉዳዩን ሲያጣራ ቆይቷል።

ሩሲያም አትሌቶቿ አበረታች መድሃኒት እንዲጠቀሙ ታደርጋለች በሚል ተደጋጋሚ ውንጀላ ሲቀርብባት ቆይቷል።

ጉዳዩን ሲያጣሩ የነበሩ አካላትም ሩሲያ አትሌቶቿ አበረታች መድሃኒት እንዲጠቀሙ አድርጋለች የሚል የምርመራ ሪፖርታቸውን አቅርበዋል።

ይህን ተከትሎም ኮሚቴው ሃገሪቱን ከውድድሩ አግዷታል።

እገዳውን ተከትሎም በቀጣዩ ጥር ወር በደቡብ ኮሪያዋ ፒዮንቻንግ በሚካሄደው የክረምት ኦሊምፒክ ላይ የማትሳተፍ ይሆናል ማለት ነው።

ይሁን እንጅ ከአበረታች መድሃኒት ንጹህ መሆናቸው የተረጋገጠ የሩሲያ አትሌቶች በውድድሩ መሳተፍ ይችላሉ።

አትሌቶቹ አበረታች መድሃኒት አለመውሰዳቸው ከተረጋገጠ ሃገራቸውን ወክለው ሳይሆን የኦሊምፒክ ተሳታፊ አትሌቶች ከሩሲያ በሚል ስም የሚሳተፉ ይሆናል።

ሩሲያ በበኩሏ እገዳውን ኮንናለች፤ አንዳንድ የሩሲያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባለስልጣናት ውሳኔውን ሲነቅፉ ሌሎች ደግሞ ስማቸውን ለማጥራት እንደሚረዳ ተናግረዋል።

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ