በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፉ 16 ክለቦች ተለይተዋል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ በቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን ያረጋገጡ 16 ክለቦች ተለይተዋል።

ትናንት ከምድብ አምስት እስከ ስምንት የተደለደሉ ክለቦች የምድብ የመጨረሻ ጨዋታቸውን አድርገዋል።

በምድብ አምስት የእንግሊዙ ሊቨርፑል በአንፊልድ ሮድ ስፓርታክ ሞስኮን አስተናግዶ 7 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በዚህም የየርገን ክሎፕ ቡድን ምድቡን በመሪነት በማጠናቀቀቅ ከፈረንጆቹ የ2008/2009 የውድድር ዘመን ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በቻምፒየንስ ሊጉ 16ቱን ክለቦች መቀላቀሉን አረጋግጧል።

ለቀያዮቹ ፊሊፔ ኮቲንሆ ሀትሪክ ሰርቷል፤ ሮቤር ፊሪሚኖ እና መሃመድ ሳላህ ሁለት ግቦችን በስማቸው ሲያስቆጥሩ፥ ሳዲዮ ማኔ ቀሪዎቹን ሁለት ግቦች ከመረብ አዋህዷል።

ማንቼስተር ሲቲ ከሜዳው ውጭ ሻክታር ዶኔስክን ገጥሞ 2 ለ 1 ተረቷል።

ሪያል ማድሪድ በሳንቲያጎ ቤርናቢዮ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን አስተናግዶ በማዮራል፣ በሉካስ ቫዝኪዩዝ እና ክርስቲያኖ ሮናልድ ግቦች 3 ለ 2 አሸንፏል።

ለዶርትሙንድ ሁለቱን ግቦች ፔር ኦበሜያንግ ነው ያስቆጠረው።

ክርስቲያኖ ሮናልዶ ቡድኑ በቻምፒየንስ ሊግ ባደረጋቸው ሁሉም የምድብ ጨዋታዎች ግብ በማስቆጠር አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል።

በዚህ የውድድር ዓመትም እስካሁን 9 የቻምፒየንስ ሊግ ግቦችን ከመረብ ያሳረፈ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ያስቆጠራቸውን ግቦች 114 አድርሷል።

የለንደኑ ቶትንሃም ሆትስፐር በዌምብሌይ አፖል ኒኮሲያን ገጥሞ 3 ለ 0 ሲረታ፥ ሰን ሄንግ ሚን፣ ኬቪን ንኮዱ እና ፈርናንዶ ሎረንቴ ግቦቹን ከመረብ አዋህደዋል።

በሌሎች የምሽቱ ጨዋታዎች ቤሺክታሽ አር ቢ ሌይፕዚግን፣ ፌይኖርድ ናፖሊን በተመሳሳይ 2 ለ 1 ሲረቱ፥ ፖርቶ በሜዳው ሞናኮን 5 ለ 2 አሸንፏል።

ሴቪያ እና ማሪቦር ያደረጉት ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በቀጣዩ ዙር የሚሳተፉ 16 ክለቦች ተለይተዋል፤

ከምድብ አንድ ማንቼስተር ዩናይትድ እና ኤፍ ሲ ባዜል፣ ከምድብ ሁለት ፓሪስ ሴንት ጀርሜይን እና ባየርሙኒክ፣ ከምድብ ሶስት ሮማ እና ቼልሲ ከምድብ አራት ደግሞ ባርሴሎና እና ጁቬንቱስ አልፈዋል።

ምድብ አምስትን ሊቨርፑል በመሪነት ሴቪያ በሁለተኛነት በማጠናቀቅ 16ቱን ክለቦች ተቀላቅለዋል።

ትናንት ከሜዳው ውጭ በሻክታር ዶኔስክ 2 ለ 1 የተሸነፈው ማንቼስተር ሲቲ ምድቡን በ15 ነጥብ በመምራት ወደ ቀጣዩ ዙር የገባ ሲሆን ሻክታር ሁለተኛ ሆኖ አልፏል።

ቤሺክታሽ እና ፖርቶ ምድብ ሰባትን አንድኛ እና ሁለተኛ ሆነው ቀጣዩን ዙር ሲቀላቀሉ፥ ምድብ ስምንት ላይ ቶትንሃም ሆትስፐር እና ሪያል ማድሪድ 16ቱን የተቀላቀሉ ቡድኖች ሆነዋል።

 

 

 

 

ምንጭ፦ቢቢሲ