ኢትዮጵያ በሴካፋ ዋንጫ በቡሩንዲ ተሸነፈች

 


አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በኬንያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የ2017 ምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቡሩንዲ አቻው 4 ለ 1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በቡክሁንጉ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው አጋማሽ 1 ለ 1 ነበር የተጠናቀቀው።

ለቡሩንዲ በ30ኛው ደቂቃ ፒየር ኩዊዜራ እና ለኢትዮጵያ ዳዋ ሁቴሳ በ45ኛ ደቂቃ አግብተው ሁለቱ ቡድኖች ለእረፍት ወጥተዋል።

ከእረፍት መልስ በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለቡሩንዲ ሴድሪክ ኡ፣ ላዲት ማቩጎ እና ሻሲር ናሂማ ተጨማሪ ሶስት ግቦችን አስቆጥረዋል።

በዚህም ዋልያዎቹ በቡሩንዲ አቻቸው 4 ለ 1 ተሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከትናንት በስቲያ ደቡብ ሱዳንን ገጥሞ 3 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።