በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ አቻ ተለያዩ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 3፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በስድስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረጉት ጨዋታ ያልምንም ግብ አቻ ተጠናቋል።


እሁድ መካሄድ የነበረበት የሸገር ደርቢ ዛሬ ማምሻውን ከ11 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተደርጓል።

6ኛ ሳምንቱን በያዘው ሊግ እስካሁን ኢትዮጵያ ቡና የዛሬውን ጨምሮ አምስት ጨዋታዋችን ያደረገ ሲሆን፥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ አራት ጨዋታዎችን አካሂዷል።

በእስካሁኑ ሂደትም ኢትዮጵያ ቡና በወልዋሎ 1 ለ 0 ሲሸነፍ፥ ሁለት አቻ ተለያይቶ ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ሁለት ጨዋታ አቻ በመለያየት ሁለቱን አሸንፏል።

ይህን ተከትሎም ሁለቱ ቡድኖች በግብ ክፍያ ተበላልጠው በእኩል ስምንት ነጥብ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 5ኛ እና 6ኛ ላይ ተቀምጠዋል።

በሁለቱ ቡድኖች በእስከዛሬው የሊግ ጨዋታ ግንኙነት ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ ክብረ ወሰን አለው።

በግንኙነታቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ 17 ጊዜ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 6 ጊዜ ማሸነፍ ችሏል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ10 ነጥቦች ሲመራ፥ ደደቢት በእኩል ነጥብ ይከተላል።

ፋሲል ከነማ እና አዳማ ከነማ በእኩል ዘጠኝ ነጥብ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

መከላከያ ደግሞ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሶስት ነጥቦችን ብቻ በመሰብሰብ የሊጉ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።