የፊፋ ተወካዮች ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር /ፊፋ/ ተወካዮች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ምርጫ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያዩ።

ፊፋ የካቲት 21 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት ለፌዴሬሽኑ በላከው ደብዳቤ በምርጫው ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ተወካዮቹን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልክ አሳውቆ ነበር።

በዚህ ምክንያት ምርጫው ለአራተኛ ጊዜ መራዘሙ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት የፊፋ ዋና መቀመጫ ከሆነችው ዙሪክ የመጡት ሚስተር ቬሮን ሞሴንጎ ኦምባ እና ሚስተር ሉካ ኒኮላ፥ ትናንት አዲስ አበባ ገብተው ከፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻህ እንደገለጹት፥ የፊፋ ተወካዮች ትናንት ከሠዓት በኋላ በምርጫው ላይ የሚሳተፉትን ባለድርሻ አካላት በግል አነጋግረዋል።

ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ እጩዎች፣ የአስመራጭ ኮሚቴና ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላትም በምርጫው ዙሪያ ከተወካዮቹ ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ሁሉንም አካላት በግል በማነጋገራቸውም በውይይቱ የተነሱትን ሀሳቦች በዝርዝር ማወቅ እንደማይቻል ጠቅሰዋል።

የፊፋ ተወካዮች ዛሬ ማለዳ ወደ ስዊዘርላንድ ያቀኑ ሲሆን፥ በተካሄደው ውይይት አማካኝነትም ፊፋ በቀጣይ ምርጫው የሚካሄድበትንና በሌሎች የምርጫው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ጠቁመዋል።

የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የውይይቱ መካሄድ የጋራ መግባባት በመፍጠር ምርጫው ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር እንደሆነም ከሁለት ሳምንት በፊት በላከው ደብዳቤ መግለጹ ኢዜአ በዘገባው አስታውሷል።