በቻምፒየንስ ሊጉ ሊቨርፑል ከማንቼስተር ሲቲ ተገናኝተዋል

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 7 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ድልድል ዛሬ ይፋ ሆኗል።

በሩብ ፍጻሜው ሁለቱ የእንግሊዝ ክለቦች ሊቨርፑልና ማንቼስተር ሲቲ እርስ በርስ ይጫወታሉ።

በሌሎች የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ባርሴሎና ከጣሊያኑ ሮማ ጋር ተገናኝቷል።

ሌላኛው የስፔን ክለብ ሲቪያ የጀርመኑን ሃያል ክለብ ባየር ሙኒክን ሲያስተናግድ፥ የአምናው የፍጻሜ ተፋላሚዎች ጁቬንቱስና ሪያል ማድሪድ በሩብ ፍጻሜው ተገናኝተዋል።

የእንግሊዞቹ ሊቨርፑልና ማንቼስተር ሲቲ በአውሮፓ መድረክ የመጀመሪያቸው የሆነው የእርስ በርስ ግንኙነት ከወዲሁ ተጠባቂ ሆኗል።

ሁለቱም ክለቦች ከድልድሉ በፊት እርስ በርስ መገናኘቱን ባይፈልጉትም ውጤቱ በተቃራኒው ሆኗል፤ በዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ባደረጉት ደርሶ መልስ ጨዋታም ተሸናንፈዋል።

ማንቼስተር ሲቲ በሜዳው 5 ለ 0 ሲያሸንፍ ሊቨርፑል ደግሞ አንፊልድ ላይ 4 ለ 3 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሎ ነበር።

በማጥቃት ላይ የተመሰረተው የሁለቱም ክለቦች አጨዋወት በሩብ ፍጻሜው ለማየት የሚያጓጓም ሆኗል።

ባርሴሎናን ከሮማ የሚያገናኘው የመጀመሪያ ጨዋታ ካምፕ ኑ ላይ ሲደረግ፥ የመልሱ በስታዲዮ ኦሊምፒኮ ይከናወናል።

በአውሮፓ መድረክ የተሻለ ታሪክ ያለው ባርሴሎና ቀለል ያለ ተጋጣሚ ያገኘ ይመስላል።

በጥሎ ማለፉ የእንግሊዙን ማንቼስተር ዩናይትድ አሸንፎ የመጣው የአንዳሉሺያው ክለብ ሲቪያ ጠንካራውን ባየር ሙኒክን ያገኘበት ድልድል ሌላው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ነው።

በአሰልጣኝ ዮፕ ሄይንክስ እየተመራ የቀድሞ አስፈሪነቱን የተላበሰው ባየር ሙኒክ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጭ ያደርጋል።

ሙኒክ በመጥፎ መልኩ የጀመረውን የውድድር አመት የቀድሞ አሰልጣኙን ካገኘ በኋላ በመቀየር ጠንካራነቱን ተላብሶ ሩብ ፍጻሜ መድረስ ችሏል።

በመድረኩም የተሻለ የአሸናፊነት ታሪክና ልምድ ባለቤት የሆኑ ተጫዋቾችን አሰባስቧል።

በአምናው የፍጻሜ ውድድር የተገናኙት ጁቬንቱስና ሪያል ማድሪድም በሩብ ፍጻሜው እርስ በርስ ይፋለማሉ።

በአውሮፓ መድረክ ሪያል ማድሪድ ከጁቬንቱስ የተሻለ ታሪክ ሲያስመዘግብ፥ አምና በዌልስ ካርዲፍ በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታም ባለድል መሆኑ ይታወሳል።

የሩብ ፍጻሜው የደርሶ መልስ የመጀመሪያ ጨዋታዎች የፊታችን መጋቢት 25 እና 26 ተደርገው የመልስ ጨዋታዎች በሳምንቱ ይከናወናሉ።